Text copied!
CopyCompare
መጽሐፍ ቅዱስ - የዮሐንስ ወንጌል - የዮሐንስ ወንጌል 11

የዮሐንስ ወንጌል 11:6-40

Help us?
Click on verse(s) to share them!
6እንደ ታመመም በሰማ ጊዜ ያን ጊዜ በነበረበት ስፍራ ሁለት ቀን ዋለ፤
7ከዚህም በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ። ወደ ይሁዳ ደግሞ እንሂድ አላቸው።
8ደቀ መዛሙርቱ። መምህር ሆይ፥ አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፥ ደግሞም ወደዚያ ትሄዳለህን? አሉት።
9ኢየሱስም መልሶ። ቀኑ አሥራ ሁለት ሰዓት አይደለምን? በቀን የሚመላለስ ቢኖር የዚህን ዓለም ብርሃን ያያልና አይሰናከልም፤
10በሌሊት የሚመላለስ ቢኖር ግን ብርሃን በእርሱ ስለ ሌለ ይሰናከላል አላቸው።
11ይህን ተናገረ፤ ከዚህም በኋላ። ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ አላቸው።
12እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ። ጌታ ሆይ፥ ተኝቶስ እንደ ሆነ ይድናል አሉት።
13ኢየሱስስ ስለ ሞቱ ተናግሮ ነበር፤ እነርሱ ግን ስለ እንቅልፍ መተኛት እንደ ተናገረ መሰላቸው።
14እንግዲህ ያን ጊዜ ኢየሱስ በግልጥ። አልዓዛር ሞተ፤
15እንድታምኑም በዚያ ባለመኖሬ ስለ እናንተ ደስ ይለኛል፤ ነገር ግን ወደ እርሱ እንሂድ አላቸው።
16ስለዚህ ዲዲሞስ የሚሉት ቶማስ ለባልንጀሮቹ ለደቀ መዛሙርት። ከእርሱ ጋር እንሞት ዘንድ እኛ ደግሞ እንሂድ አለ።
17ኢየሱስም በመጣ ጊዜ በመቃብር እስከ አሁን አራት ቀን ሆኖት አገኘው።
18ቢታንያም አሥራ አምስት ምዕራፍ ያህል ለኢየሩሳሌም ቅርብ ነበረች።
19ከአይሁድም ብዙዎች ስለ ወንድማቸው ሊያጽናኑአቸው ወደ ማርታና ወደ ማርያም መጥተው ነበር።
20ማርታም ኢየሱስ እንደ መጣ በሰማች ጊዜ ልትቀበለው ወጣች፤ ማርያም ግን በቤት ተቀምጣ ነበር።
21ማርታም ኢየሱስን። ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር፤
22አሁንም ከእግዚአብሔር የምትለምነውን ሁሉ እግዚአብሔር እንዲሰጥህ አውቃለሁ አለችው።
23ኢየሱስም። ወንድምሽ ይነሣል አላት።
24ማርታም። በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ አለችው።
25ኢየሱስም። ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤
26ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት።
27እርስዋም። አዎን ጌታ ሆይ፤ አንተ ወደ ዓለም የሚመጣው ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆንህ እኔ አምናለሁ አለችው።
28ይህንም ብላ ሄደች እኅትዋንም ማርያምን በስውር ጠርታ። መምህሩ መጥቶአል ይጠራሽማል አለቻት።
29እርስዋም በሰማች ጊዜ ፈጥና ተነሣች ወደ እርሱም መጣች፤
30ኢየሱስም ማርታ በተቀበለችበት ስፍራ ነበረ እንጂ ገና ወደ መንደሩ አልገባም ነበር።
31ሲያጽናኑአት ከእርስዋ ጋር በቤት የነበሩ አይሁድም ማርያም ፈጥና እንደ ተነሣችና እንደ ወጣች ባዩ ጊዜ፥ ወደ መቃብር ሄዳ በዚያ ልታለቅስ መስሎአቸው ተከተሉአት።
32ማርያምም ኢየሱስ ወዳለበት መጥታ ባየችው ጊዜ በእግሩ ላይ ወድቃ። ጌታ ሆይ፥ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር አለችው።
33ኢየሱስም እርስዋ ስታለቅስ ከእርስዋም ጋር የመጡት አይሁድ ሲያለቅሱ አይቶ በመንፈሱ አዘነ በራሱም ታወከ፤
34ወዴት አኖራችሁት? አለም። እነርሱም። ጌታ ሆይ፥ መጥተህ እይ አሉት።
35ኢየሱስም እንባውን አፈሰሰ።
36ስለዚህ አይሁድ። እንዴት ይወደው እንደ ነበረ እዩ አሉ።
37ከእነርሱ ግን አንዳንዶቹ። ይህ የዕውሩን ዓይኖች የከፈተ ይህን ደግሞ እንዳይሞት ያደርግ ዘንድ ባልቻለም ነበርን? አሉ።
38ኢየሱስም በራሱ አዝኖ ወደ መቃብሩ መጣ፤ እርሱም ዋሻ ነበረ፤ ድንጋይም ተገጥሞበት ነበር።
39ኢየሱስ። ድንጋዩን አንሡ አለ። የሞተውም እኅት ማርታ። ጌታ ሆይ፥ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል አለችው።
40ኢየሱስ። ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን? አላት።

Read የዮሐንስ ወንጌል 11የዮሐንስ ወንጌል 11
Compare የዮሐንስ ወንጌል 11:6-40የዮሐንስ ወንጌል 11:6-40