Text copied!
CopyCompare
መጽሐፍ ቅዱስ - የሉቃስ ወንጌል - የሉቃስ ወንጌል 9

የሉቃስ ወንጌል 9:31-62

Help us?
Click on verse(s) to share them!
31በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር።
32ነገር ግን ጴጥሮስንና ከእርሱ ጋር የነበሩት እንቅልፍ ከበደባቸው፤ ነቅተው ግን ክብሩንና ከእርሱ ጋር ቆመው የነበሩትን ሁለት ሰዎች አዩ።
33ከእርሱም ሲለዩ ጴጥሮስ ኢየሱስን። አቤቱ፥ በዚህ መሆን ለእኛ መልካም ነውና አንድ ለአንተ አንድም ለሙሴ አንድም ለኤልያስ ሦስት ዳሶች እንሥራ አለው፤ የሚለውንም አያውቅም ነበር።
34ይህንም ሲናገር ደመና መጣና ጋረዳቸው፤ ወደ ደመናውም ሲገቡ ሳሉ ፈሩ።
35ከደመናውም። የመረጥሁት ልጄ ይህ ነው፥ እርሱን ስሙት የሚል ድምፅ መጣ።
36ድምፁም ከመጣ በኋላ ኢየሱስ ብቻውን ሆኖ ተገኘ። እነርሱም ዝም አሉ ካዩትም ነገር በዚያ ወራት ምንም ለማንም አላወሩም።
37በነገውም ከተራራ ሲወርዱ ብዙ ሕዝብ ተገናኙት።
38እነሆም፥ ከሕዝቡ አንድ ሰው እንዲህ እያለ ጮኸ። መምህር ሆይ፥ ለእኔ አንድ ልጅ ነውና ልጄን እንድታይልኝ እለምንሃለሁ።
39እነሆም፥ ጋኔን ይይዘዋል፥ ድንገትም ይጮኻል አረፋም እያስደፈቀው ያንፈራግጠዋል፥ እየቀጠቀጠም በጭንቅ ይለቀዋል፤
40ደቀ መዛሙርትህንም እንዲያወጡት ለመንሁ፥ አልቻሉምም።
41ኢየሱስም መልሶ። እናንተ የማታምን ጠማማ ትውልድ፥ እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? ልጅህን ወደዚህ አምጣው አለ።
42ሲቀርብም ጋኔኑ ጣለውና አንፈራገጠው፤ ኢየሱስ ግን ርኵሱን መንፈስ ገሥጾ ብላቴናውን ፈወሰው ለአባቱም መለሰው።
43ሁሉም ከእግዚአብሔር ታላቅነት የተነሣ ተገረሙ። ሁሉም ኢየሱስ ባደረገው ሁሉ ሲደነቁ፥
44ለደቀ መዛሙርቱ። የሰው ልጅ በሰው እጅ ይሰጥ ዘንድ አለውና እናንተ ይህን ቃል በጆሮአችሁ አኑሩ አለ።
45እነርሱ ግን ይህን ነገር አላስተዋሉም፥ እንዳይገባቸውም ተሰውሮባቸው ነበር፤ ስለዚህ ነገርም እንዳይጠይቁት ፈሩ።
46ከእነርሱም ማን እንዲበልጥ ክርክር ተነሣባቸው።
47ኢየሱስም የልባቸውን አሳብ አውቆ ሕፃንን ያዘ፤ በአጠገቡም አቁሞ።
48ማንም ይህን ሕፃን በስሜ የሚቀበል እኔን ይቀበላል፤ የሚቀበለኝም ሁሉ የላከኝን ይቀበላል፤ ከሁላችሁ የሚያንስ እርሱ ታላቅ ነውና አላቸው።
49ዮሐንስም መልሶ። አቤቱ፥ አንድ ሰው በስምህ አጋንንትን ሲያወጣ አየነው፥ ከእኛ ጋርም ስለማይከተል ከለከልነው አለው።
50ኢየሱስ ግን። የማይቃወማችሁ ከእናንተ ጋር ነውና አትከልክሉት አለው።
51የሚወጣበትም ወራት በቀረበ ጊዜ ወደ ኢየሩሳሌም ለመሄድ ፊቱን አቀና፥
52በፊቱም መልክተኞችን ሰደደ። ሄደውም ሊያሰናዱለት ወደ አንድ ወደ ሳምራውያን መንደር ገቡ፤
53ፊቱም ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚሄድ ስለ ነበረ አልተቀበሉትም።
54ደቀ መዛሙርቱም ያዕቆብና ዮሐንስ አይተው። ጌታ ሆይ፥ ኤልያስ ደግሞ እንዳደረገ እሳት ከሰማይ ወርዶ ያጥፋቸው እንል ዘንድ ትወዳለህን? አሉት።
55እርሱ ግን ዘወር ብሎ ገሠጻቸውና። ምን ዓይነት መንፈስ እንደ ሆነላችሁ አታውቁም፤
56የሰው ልጅ የሰውን ነፍስ ሊያድን እንጂ ሊያጠፋ አልመጣም አለ። ወደ ሌላ መንደርም ሄዱ።
57እነርሱም በመንገድ ሲሄዱ አንድ ሰው። ጌታ ሆይ፥ ወደ ምትሄድበት ሁሉ እከተልሃለሁ አለው።
58ኢየሱስም። ለቀበሮዎች ጕድጓድ ለሰማይም ወፎች መሳፈሪያ አላቸው፥ ለሰው ልጅ ግን ራሱን የሚያስጠጋበት የለውም አለው።
59ሌላውንም። ተከተለኝ አለው። እርሱ ግን። ጌታ ሆይ፥ አስቀድሜ ልሂድና አባቴን እቀብር ዘንድ ፍቀድልኝ አለ።
60ኢየሱስም። ሙታናቸውን እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤ አንተስ ሄደህ የእግዚአብሔርን መንግሥት ስበክ አለው።
61ደግሞ ሌላው። ጌታ ሆይ፥ እከተልሃለሁ፤ ነገር ግን አስቀድሜ ከቤቴ ሰዎች እንድሰናበት ፍቀድልኝ አለ።
62ኢየሱስ ግን። ማንም ዕርፍ በእጁ ይዞ ወደ ኋላ የሚመለከት ለእግዚአብሔር መንግሥት የተገባ አይደለም አለው።

Read የሉቃስ ወንጌል 9የሉቃስ ወንጌል 9
Compare የሉቃስ ወንጌል 9:31-62የሉቃስ ወንጌል 9:31-62