Text copied!
CopyCompare
መጽሐፍ ቅዱስ - የማርቆስ ወንጌል - የማርቆስ ወንጌል 6

የማርቆስ ወንጌል 6:30-55

Help us?
Click on verse(s) to share them!
30ሐዋርያትም ወደ ኢየሱስ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት።
31እናንት ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ አላቸው፤ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩና፥ ለመብላት እንኳ ጊዜ አጡ።
32በታንኳውም ብቻቸውን ወደ ምድረ በዳ ሄዱ።
33ሰዎችም ሲሄዱ አዩአቸው ብዙዎችም አወቁአቸውና ከከተሞች ሁሉ በእግር እየሮጡ ወዲያ ቀደሙአቸው ወደ እርሱም ተሰበሰቡ።
34ኢየሱስም ወጥቶ ብዙ ሕዝብ አየና እረኛ እንደሌላቸው በጎች ስለ ነበሩ አዘነላቸው፥ ብዙም ነገር ያስተምራቸው ጀመር።
35በዚያን ጊዜም ብዙ ሰዓት ካለፈ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ወደ እርሱ ቀርበው። ቦታው ምድረ በዳ ነው አሁንም መሽቶአል፤
36የሚበሉት የላቸውምና በዙሪያ ወዳሉ ገጠሮችና መንደሮች ሄደው እንጀራ ለራሳቸው እንዲገዙ አሰናብታቸው አሉት።
37እርሱ ግን መልሶ። እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው አላቸው። ሄደን እንጀራ በሁለት መቶ ዲናር እንግዛላቸውን? እንዲበሉም እንስጣቸውን? አሉት።
38እርሱም። ስንት እንጀራ አላችሁ? ሂዱና እዩ አላቸው። ባወቁም ጊዜ። አምስት፥ ሁለትም ዓሣ አሉት።
39ሁሉንም በየክፍሉ በለመለመ ሣር ላይ እንዲያስቀምጡአቸው አዘዛቸው።
40መቶ መቶውና አምሳ አምሳው እየሆኑ በተራ በተራ ተቀመጡ።
41አምስቱንም እንጀራ ሁለቱንም ዓሣ ይዞ ወደ ሰማይ አሻቅቦ አየና ባረከ፥ እንጀራውንም ቈርሶ እንዲያቀርቡላቸው ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠ፥
42ሁለቱን ዓሣ ደግሞ ለሁሉ ከፈለ። ሁሉም በልተው ጠገቡ፤
43ከቍርስራሹም አሥራ ሁለት መሶብ የሞላ አነሡ ከዓሣውም ደግሞ።
44እንጀራውንም የበሉት ወንዶቹ አምስት ሺህ ነበሩ።
45ወዲያውም ሕዝቡን ሲያሰናብት ሳለ ደቀ መዛሙርቱ በታንኳ ገብተው ወደ ማዶ ወደ ቤተ ሳይዳ እንዲቀድሙት ግድ አላቸው።
46ካሰናበታቸውም በኋላ ሊጸልይ ወደ ተራራ ወጣ።
47በመሸም ጊዜ ታንኳይቱ በባሕር መካከል ሳለች እርሱ ብቻውን በምድር ላይ ነበረ።
48ነፋስ ወደ ፊታቸው ነበረና እየቀዘፉ ሲጨነቁ አይቶ፥ ከሌሊቱ በአራተኛው ክፍል በባሕር ላይ እየሄደ ወደ እነርሱ መጣ፤ ሊያልፋቸውም ይወድ ነበር።
49እነርሱ ግን በባሕር ላይ ሲሄድ ባዩት ጊዜ ምትሀት መሰላቸውና ጮኹ፥
50ሁሉ አይተውታልና፥ ታወኩም። ወዲያውም ተናገራቸውና። አይዞአችሁ፤ እኔ ነኝ፥ አትፍሩ አላቸው።
51ወደ እነርሱም ወደ ታንኳይቱ ገባ፥ ነፋሱም ተወ፤ በራሳቸውም ያለ መጠን እጅግ ተገረሙ፤
52ስለ እንጀራው አላስተዋሉምና፤ ነገር ግን ልባቸው ደንዝዞ ነበር።
53ተሻግረውም ወደ ምድር ወደ ጌንሴሬጥ ደረሱ ታንኳይቱንም አስጠጉ።
54ከታንኳይቱም ሲወጡ ወዲያው አውቀውት
55በዚያች አገር ሁሉ ዙሪያ ሮጡና እርሱ እንዳለ ወደ ሰሙበት ስፍራ ሕመምተኞችን በአልጋ ላይ ያመጡ ጀመር።

Read የማርቆስ ወንጌል 6የማርቆስ ወንጌል 6
Compare የማርቆስ ወንጌል 6:30-55የማርቆስ ወንጌል 6:30-55