Text copied!
CopyCompare
መጽሐፍ ቅዱስ - 1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች

1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13

Help us?
Click on verse(s) to share them!
1በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ ጸናጽል ሆኜአለሁ።
2ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና እውቀትን ሁሉ ባውቅ፥ ተራሮችንም እስካፈልስ ድረስ እምነት ሁሉ ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ።
3ድሆችንም ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል፥ ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም።
4ፍቅር ይታገሣል፥ ቸርነትንም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፥ አይታበይም፤
5የማይገባውን አያደርግም፥ የራሱንም አይፈልግም፥ አይበሳጭም፥ በደልን አይቆጥርም፤
6ከእውነት ጋር ደስ ይለዋል እንጂ ስለ ዓመፃ ደስ አይለውም፤
7ሁሉን ይታገሣል፥ ሁሉን ያምናል፥ ሁሉን ተስፋ ያደርጋል፥ በሁሉ ይጸናል።
8ፍቅር ለዘወትር አይወድቅም፤ ትንቢት ቢሆን ግን ይሻራል፤ ልሳኖች ቢሆኑ ይቀራሉ፤ እውቀትም ቢሆን ይሻራል።
9ከእውቀት ከፍለን እናውቃለንና፥ ከትንቢትም ከፍለን እንናገራለንና፤
10ፍጹም የሆነ ሲመጣ ግን ተከፍሎ የነበረው ይሻራል።
11ልጅ ሳለሁ እንደ ልጅ እናገር ነበር፥ እንደ ልጅም አስብ ነበር፥ እንደ ልጅም እቈጥር ነበር፤ ጎልማሳ ሆኜ ግን የልጅነትን ጠባይ ሽሬአለሁ።
12ዛሬስ በመስተዋት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን፤ ዛሬስ ከእውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደ ታወቅሁ አውቃለሁ።
13እንዲህም ከሆነ፥ እምነት ተስፋ ፍቅር እነዚህ ሦስቱ ጸንተው ይኖራሉ፤ ከእነዚህም የሚበልጠው ፍቅር ነው።