29ርኵሱን መንፈስ ከሰውዬው እንዲወጣ ያዘው ነበርና። ብዙ ዘመንም ይዞት ነበርና፥ በሰንሰለትና በእግር ብረትም ታስሮ ይጠበቅ ነበር፤ እስራቱንም ሰብሮ በጋኔኑ ወደ ምድረ በዳ ይነዳ ነበር።
30ኢየሱስም። ስምህ ማን ነው? ብሎ ጠየቀው። እርሱም ብዙዎች አጋንንት ገብተውበት ነበርና። ሌጌዎን አለው።
31ወደ ጥልቁም ሊሄዱ እንዳያዛቸው ለመኑት።
32በዚያም በተራራው የብዙ እሪያ መንጋ ይሰማሩ ነበር፤ ወደ እነርሱም ሊገቡ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት፤ ፈቀደላቸውም።
33አጋንንትም ከሰውዬው ወጥተው ወደ እሪያዎች ገቡ፥ መንጋውም ከአፋፉ ወደ ባሕር ተጣደፉና ሰጠሙ።
34እረኞችም የሆነውን ባዩ ጊዜ ሸሽተው በከተማውና በአገሩ አወሩት።
35የሆነውን ነገር ሊያዩ ወጥተውም ወደ ኢየሱስ መጡ፥ አጋንንትም የወጡለትን ሰው ለብሶ ልቡም ተመልሶ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ አገኙትና ፈሩ።
36ያዩትም ደግሞ አጋንንት ያደሩበት ሰው እንዴት እንደ ዳነ አወሩላቸው።
37በዙሪያውም በጌርጌሴኖን አገር ያሉት ሕዝብ ሁሉ ታላቅ ፍርሃት ይዞአቸዋልና ከእነርሱ እንዲሄድ ለመኑት በታንኳም ገብቶ ተመለሰ።
38አጋንንት የወጡለት ሰውም ከእርሱ ጋር ይኖር ዘንድ ለመነው፤
39ነገር ግን። ወደ ቤትህ ተመለስ፥ እግዚአብሔር እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረግልህ ንገር ብሎ አሰናበተው። ኢየሱስም እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት በከተማው ሁሉ እየሰበከ ሄደ።
40ኢየሱስም በተመለሰ ጊዜ ሁሉ ይጠብቁት ነበርና ሕዝቡ ተቀበሉት።
41እነሆም፥ ኢያኢሮስ የሚባል ሰው መጣ፥ እርሱም የምኵራብ አለቃ ነበረ በኢየሱስም እግር ላይ ወድቆ ወደ ቤቱ እንዲገባ ለመነው፤
42አሥራ ሁለት ዓመት የሆናት አንዲት ሴት ልጅ ነበረችውና፤ እርስዋም ለሞት ቀርባ ነበረች። ሲሄድም ሕዝቡ ያጨናንቁት ነበር።
43ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፥ ትዳርዋንም ሁሉ ለባለመድኃኒቶች ከስራ ማንም ሊፈውሳት አልተቻለውም።
44በኋላውም ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፥ የደምዋም ፈሳሽ በዚያን ጊዜ ቆመ።
45ኢየሱስም። የዳሰሰኝ ማን ነው? አለ። ሁሉም በካዱ ጊዜ፥ ጴጥሮስና ከእርሱ ጋር የነበሩት። አቤቱ፥ ሕዝቡ ያጫንቁሃልና ያጋፉህማል፤ የዳሰሰኝ ማን ነው ትላለህን? አሉ።
46ኢየሱስ ግን። አንድ ሰው ዳስሶኛል፥ ኃይል ከእኔ እንደ ወጣ እኔ አውቃለሁና አለ።
47ሴቲቱም እንዳልተሰወረች ባየች ጊዜ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፥ በምን ምክንያትም እንደ ዳሰሰችው ፈጥናም እንደ ተፈወሰች በሕዝቡ ሁሉ ፊት አወራች።
48እርሱም። ልጄ ሆይ፥ እምነትሽ አድኖሻል፤ በሰላም ሂጂ አላት።
49እርሱም ገና ሲናገር አንድ ሰው ከምኵራብ አለቃው ቤት መጥቶ። ልጅህ ሞታለች፤ እንግዲህ መምህሩን አታድክም አለ።
50ኢየሱስ ግን ሰምቶ። አትፍራ፤ እመን ብቻ ትድንማለች ብሎ መለሰለት።
51ወደ ቤትም ሲገባ ከጴጥሮስና ከያዕቆብ ከዮሐንስም ከብላቴናይቱም አባትና እናት በቀር ማንም ከእርሱ ጋር ይገባ ዘንድ አልፈቀደም።
52ሁሉም እያለቀሱላት ዋይ ዋይ ይሉ ነበር። እርሱ ግን። አታልቅሱ፤ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም አለ።
53እንደ ሞተችም አውቀው በጣም ሳቁበት።
54እርሱ ግን እጅዋን ይዞ። አንቺ ብላቴና፥ ተነሺ ብሎ ጮኸ።