2የአይሁድም የዳስ በዓል ቀርቦ ነበር።
3እንግዲህ ወንድሞቹ። ደቀ መዛሙርትህ ደግሞ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ፤
4ራሱ ሊገለጥ እየፈለገ በስውር የሚሠራ የለምና። እነዚህን ብታደርግ ራስህን ለዓለም ግለጥ አሉት።
5ወንድሞቹ ስንኳ አላመኑበትም ነበርና።
6ኢየሱስም እንዲህ አላቸው። ጊዜዬ ገና አልደረሰም፥ ጊዜያችሁ ግን ዘወትር የተመቸ ነው።
7ዓለም እናንተን ሊጠላ አይቻለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ መሆኑን እመሰክርበታለሁና እኔን ይጠላኛል።
8እናንተ ወደዚህ በዓል ውጡ፤ እኔስ ጊዜዬ ገና ስላልተፈጸመ ወደዚህ በዓል ገና አልወጣም።
9ይህንም አላቸውና በገሊላ ቀረ።
10ወንድሞቹ ግን ወደ በዓሉ ከወጡ በኋላ በዚያን ጊዜ እርሱ ደግሞ በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ወጣ።
11አይሁድም። እርሱ ወዴት ነው? እያሉ በበዓሉ ይፈልጉት ነበር።
12በሕዝብም መካከል ስለ እርሱ ብዙ ማንጐራጐር ነበረ፤ አንዳንዱም። ደግ ሰው ነው፤ ሌሎች ግን። አይደለም፥ ሕዝቡን ግን ያስታል ይሉ ነበር።