13እነርሱም። አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? አሉአት። እርስዋም። ጌታዬን ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አላውቅም አለቻቸው።
14ይህንም ብላ ወደ ኋላ ዘወር ስትል ኢየሱስን ቆሞ አየችው፤ ኢየሱስም እንደ ሆነ አላወቀችም።
15ኢየሱስም። አንቺ ሴት፥ ስለ ምን ታለቅሻለሽ? ማንንስ ትፈልጊያለሽ? አላት። እርስዋም የአትክልት ጠባቂ መስሎአት። ጌታ ሆይ፥ አንተ ወስደኸው እንደ ሆንህ ወዴት እንዳኖርኸው ንገረኝ እኔም እወስደዋለሁ አለችው።
16ኢየሱስም። ማርያም አላት። እርስዋ ዘወር ብላ በዕብራይስጥ። ረቡኒ አለችው፤ ትርጓሜውም። መምህር ሆይ ማለት ነው።
17ኢየሱስም። ገና ወደ አባቴ አላረግሁምና አትንኪኝ፤ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ። እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ ዓርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት።
18መግደላዊት ማርያም መጥታ ጌታን እንዳየች ይህንም እንዳላት ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች።