15ከዚያም ወንድሞች ስለ እኛ ሰምተው እስከ አፍዩስ ፋሩስና ሦስት ማደሪያ እስከሚባለው ሊቀበሉን ወጡ፥ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ ልቡም ተጽናና።
16ወደ ሮሜም በገባን ጊዜ ጳውሎስ ከሚጠብቀው ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ተፈቀደለት።
17ከሦስት ቀንም በኋላ ጳውሎስ የአይሁድን ታላላቆች ወደ እርሱ ጠራ፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ሕዝቡን ወይም የአባቶችን ሥርዓት የሚቃወም አንዳች ሳላደርግ፥ ከኢየሩሳሌም እንደ ታሰርሁ በሮማውያን እጅ አሳልፈው ሰጡኝ።
18እነርሱም መርምረው ለሞት የሚገባ ምክንያት ስላልነበረብኝ ሊፈቱኝ አሰቡ፤
19አይሁድ ግን በተቃወሙ ጊዜ፥ ወደ ቄሣር ይግባኝ እንድል ግድ ሆነብኝ እንጂ ሕዝቤን የምከስበት ነገር ኖሮኝ አይደለም።
20ስለዚህም ምክንያት አያችሁና እነግራችሁ ዘንድ ጠራኋችሁ፤ ስለ እስራኤል ተስፋ ይህን ሰንሰለት ለብሻለሁና።
21እነርሱም። እኛ ከይሁዳ ስለ አንተ ደብዳቤ አልተቀበልንም፥ ከወንድሞችም አንድ ስንኳ መጥቶ ስለ አንተ ክፉ ነገር አላወራልንም ወይም አልተናገረብህም።