60ከደቀ መዛሙርቱም ብዙዎች በሰሙ ጊዜ። ይህ የሚያስጨንቅ ንግግር ነው፤ ማን ሊሰማው ይችላል? አሉ።
61ኢየሱስ ግን ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ እንዳንጐራጐሩ በልቡ አውቆ አላቸው። ይህ ያሰናክላችኋልን?
62እንግዲህ የሰው ልጅ አስቀድሞ ወደ ነበረበት ሲወጣ ብታዩ እንዴት ይሆናል?
63ሕይወትን የሚሰጥ መንፈስ ነው፤ ሥጋ ምንም አይጠቅምም፤ እኔ የነገርኋችሁ ቃል መንፈስ ነው ሕይወትም ነው።
64ነገር ግን ከእናንተ የማያምኑ አሉ። ኢየሱስ የማያምኑት እነማን እንደ ሆኑ አሳልፎ የሚሰጠውም ማን እንደ ሆነ ከመጀመሪያ ያውቅ ነበርና።
65ደግሞ። ስለዚህ አልኋችሁ፥ ከአብ የተሰጠው ካልሆነ ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም አለ።
66ከዚህም የተነሣ ከደቀ መዛሙርቱ ብዙዎች ወደ ኋላ ተመለሱ፤ ወደ ፊትም ከእርሱ ጋር አልሄዱም።