17ዓለም በልጁ እንዲድን ነው እንጂ፥ በዓለም እንዲፈርድ እግዚአብሔር ወደ ዓለም አልላከውምና።
18በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።
19ብርሃንም ወደ ዓለም ስለ መጣ ሰዎችም ሥራቸው ክፉ ነበርና ከብርሃን ይልቅ ጨለማን ስለ ወደዱ ፍርዱ ይህ ነው።
20ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤
21እውነትን የሚያደርግ ግን ሥራው በእግዚአብሔር ተደርጎ እንደ ሆነ ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል።
22ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ አገር መጣ፥ በዚያም ከእነርሱ ጋር ተቀምጦ ያጠምቅ ነበር።
23ዮሐንስም ደግሞ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና ያጠምቅ ነበር፥
24እየመጡም ይጠመቁ ነበር ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ አልተጨመረም ነበርና።
25ስለዚህም በዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና በአይሁድ መካከል ስለ ማንጻት ክርክር ሆነ።
26ወደ ዮሐንስም መጥተው። መምህር ሆይ፥ በዮርዳኖስ ማዶ ከአንተ ጋር የነበረው አንተም የመሰከርህለት፥ እነሆ፥ እርሱ ያጠምቃል ሁሉም ወደ እርሱ ይመጣሉ አሉት።
27ዮሐንስ መለሰ፥ እንዲህ ሲል። ከሰማይ ካልተሰጠው ሰው እንዳች ሊቀበል አይችልም።
28እናንተ። እኔ ክርስቶስ አይደለሁም፥ ነገር ግን። ከእርሱ በፊት ተልኬአለሁ እንዳልሁ ራሳችሁ ትመሰክሩልኛላችሁ።