8ስለዚህ ጲላጦስ ይህን ነገር በሰማ ጊዜ እግጅ ፈራ፤
9ተመልሶም ወደ ገዡ ግቢ ገባና ኢየሱስን። አንተ ከወዴት ነህ? አለው። ኢየሱስ ግን አንድ እንኳ አልመለሰለትም።
10ስለዚህ ጲላጦስ። አትነግረኝምን? ልሰቅልህ ሥልጣን እንዳለኝ ወይም ልፈታህ ሥልጣን እንዳለኝ አታውቅምን? አለው።
11ኢየሱስም መልሶ። ከላይ ካልተሰጠህ በቀር በእኔ ላይ ምንም ሥልጣን ባልነበረህም፤ ስለዚህ ለአንተ አሳልፎ የሰጠኝ ኃጢአቱ የባሰ ነው አለው።
12ከዚህ በኋላ ጲላጦስ ሊፈታው ፈለገ፤ ነገር ግን አይሁድ። ይህንስ ብትፈታው የቄሣር ወዳጅ አይደለህም፤ ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሁሉ የቄሣር ተቃዋሚ ነው እያሉ ጮኹ።
13ጲላጦስም ይህን ነገር ሰምቶ ኢየሱስን ወደ ውጭ አወጣው፥ በዕብራይስጥም ገበታ በተባለው ጸፍጸፍ በሚሉት ስፍራ በፍርድ ወንበር ተቀመጠ።
14ለፋሲካም የማዘጋጀት ቀን ነበረ፤ ስድስት ሰዓትም የሚያህል ነበረ፤ አይሁድንም። እነሆ ንጉሣችሁ አላቸው።