12በመንገድ ዳርም ያሉት የሚሰሙ ናቸው፤ ከዚህ በኋላም ዲያብሎስ ይመጣል አምነውም እንዳይድኑ ቃሉን ከልባቸው ይወስዳል።
13በዓለት ላይም ያሉት ሲሰሙ ቃሉን በደስታ የሚቀበሉ ናቸው፤ እነርሱም ለጊዜው ብቻ ያምናሉ እንጂ በፈተና ጊዜ የሚክዱ ሥር የሌላቸው ናቸው።
14በእሾህ መካከልም የወደቀ እነዚህ የሚሰሙት ናቸው፤ መንገዳቸውንም ሄደው በሕይወት ዘመን በአሳብና በባለ ጠግነት ምቾት ይታነቃሉ፥ ሙሉ ፍሬም አያፈሩም።
15በመልካም መሬት ላይም የወደቀ እነርሱ በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።
16መብራትንም አብርቶ በዕቃ የሚከድነው ወይም ከአልጋ በታች የሚያኖረው የለም፥ የሚገቡት ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል እንጂ።
17የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፥ የማይታወቅም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተሸሸገ የለም።
18እንግዲህ እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና፥ ከሌለውም ሁሉ፥ ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።
19እናቱና ወንድሞቹም ወደ እርሱ መጡ፥ ከሕዝቡም ብዛት የተነሣ ሊያገኙት አልተቻላቸውም።
20እናትህና ወንድሞችህ ሊያዩህ ወድደው በውጭ ቆመዋል ብለው ነገሩት።
21እርሱም መልሶ። እናቴና ወንድሞቼስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት እነዚህ ናቸው አላቸው።
22ከዕለታቱም በአንዱ እርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳ ገብቶ። ወደ ባሕር ማዶ እንሻገር አላቸው፤ ተነሡም።
23ሲሄዱም አንቀላፋ። ዓውሎ ነፋስም በባሕር ላይ ወረደ፥ ውኃውም ታንኳይቱን ይሞላ ነበርና ይጨነቁ ነበር።
24ቀርበውም። አቤቱ፥ አቤቱ ጠፋን እያሉ አስነሡት። እርሱም ነቅቶ ነፋሱንና የውኃውን ማዕበል ገሠጻቸው፤ ተዉም፥ ጽጥታም ሆነ።
25እርሱም። እምነታችሁ የት ነው? አላቸው። ፈርተውም ተደነቁ፥ እርስ በርሳቸውም። እንዲህ ነፋሳትንና ውኃን እንኳ የሚያዝ ለእርሱም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው? አሉ።
26በገሊላም አንጻር ወዳለችው ወደ ጌርጌሴኖን አገር በታንኳ ደረሱ።
27ወደ ምድርም በወጣ ጊዜ አጋንንት ያደሩበት አንድ ሰው ከከተማ ወጥቶ ተገናኘው፥ ከብዙ ዘመንም ጀምሮ ልብስ ሳይለብስ በመቃብር እንጂ በቤት አይኖርም ነበር።
28ኢየሱስንም ባየ ጊዜ ጮኾ በፊቱ ተደፋ በታላቅ ድምፅም። የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳትሣቀየኝ እለምንሃለሁ አለ።
29ርኵሱን መንፈስ ከሰውዬው እንዲወጣ ያዘው ነበርና። ብዙ ዘመንም ይዞት ነበርና፥ በሰንሰለትና በእግር ብረትም ታስሮ ይጠበቅ ነበር፤ እስራቱንም ሰብሮ በጋኔኑ ወደ ምድረ በዳ ይነዳ ነበር።
30ኢየሱስም። ስምህ ማን ነው? ብሎ ጠየቀው። እርሱም ብዙዎች አጋንንት ገብተውበት ነበርና። ሌጌዎን አለው።
31ወደ ጥልቁም ሊሄዱ እንዳያዛቸው ለመኑት።
32በዚያም በተራራው የብዙ እሪያ መንጋ ይሰማሩ ነበር፤ ወደ እነርሱም ሊገቡ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት፤ ፈቀደላቸውም።
33አጋንንትም ከሰውዬው ወጥተው ወደ እሪያዎች ገቡ፥ መንጋውም ከአፋፉ ወደ ባሕር ተጣደፉና ሰጠሙ።
34እረኞችም የሆነውን ባዩ ጊዜ ሸሽተው በከተማውና በአገሩ አወሩት።
35የሆነውን ነገር ሊያዩ ወጥተውም ወደ ኢየሱስ መጡ፥ አጋንንትም የወጡለትን ሰው ለብሶ ልቡም ተመልሶ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ አገኙትና ፈሩ።
36ያዩትም ደግሞ አጋንንት ያደሩበት ሰው እንዴት እንደ ዳነ አወሩላቸው።
37በዙሪያውም በጌርጌሴኖን አገር ያሉት ሕዝብ ሁሉ ታላቅ ፍርሃት ይዞአቸዋልና ከእነርሱ እንዲሄድ ለመኑት በታንኳም ገብቶ ተመለሰ።
38አጋንንት የወጡለት ሰውም ከእርሱ ጋር ይኖር ዘንድ ለመነው፤
39ነገር ግን። ወደ ቤትህ ተመለስ፥ እግዚአብሔር እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረግልህ ንገር ብሎ አሰናበተው። ኢየሱስም እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት በከተማው ሁሉ እየሰበከ ሄደ።
40ኢየሱስም በተመለሰ ጊዜ ሁሉ ይጠብቁት ነበርና ሕዝቡ ተቀበሉት።