4 በነጋም ጊዜ ኢየሱስ በባሕር ዳር ቆመ፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን ኢየሱስ መሆኑን አላወቁም።
5 ኢየሱስም። ልጆች ሆይ፥ አንዳች የሚበላ አላችሁን? አላቸው። የለንም ብለው መለሱለት።
6 እርሱም። መረቡን በታንኳይቱ በስተ ቀኝ ጣሉት ታገኙማላችሁ አላቸው። ስለዚህ ጣሉት፤ በዚህም ጊዜ ከዓሣው ብዛት የተነሣ ሊጐትቱት አቃታቸው።
7 ኢየሱስ ይወደው የነበረውም ደቀ መዝሙር ጴጥሮስን። ጌታ እኮ ነው አለው። ስለዚህ ስምዖን ጴጥሮስ ጌታ መሆኑን በሰማ ጊዜ ዕራቁቱን ነበረና ልብሱን ታጥቆ ወደ ባሕር ራሱን ጣለ።
8 ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ግን ከምድር ሁለት መቶ ክንድ ያህል እንጂ እጅግ አልራቁም ነበርና ዓሣ የሞላውን መረብ እየሳቡ በጀልባ መጡ።
9 ወደ ምድርም በወጡ ጊዜ ፍምና ዓሣ በላዩ ተቀምጦ እንጀራም አዩ።
10 ኢየሱስም። አሁን ካጠመዳችሁት ዓሣ አምጡ አላቸው።
11 ስምዖን ጴጥሮስም ወደ ጀልባይቱ ገብቶ መቶ አምሳ ሦስት ታላላቅ ዓሦች ሞልቶ የነበረውን መረብ ወደ ምድር ጐተተ፤ ይህንም ያህል ብዙ ሲሆን መረቡ አልተቀደደም።