Text copied!
Bibles in Amharic

የዮሐንስ ወንጌል 19:22-40 in Amharic

Help us?

የዮሐንስ ወንጌል 19:22-40 in መጽሐፍ ቅዱስ

22 ጲላጦስም። የጻፍሁትን ጽፌአለሁ ብሎ መለሰ።
23 ጭፍሮችም ኢየሱስን በሰቀሉት ጊዜ ልብሶቹን ወስደው ለእያንዳንዱ ጭፍራ አንድ ክፍል ሆኖ በአራት ከፋፈሉት፤ እጀጠባቡን ደግሞ ወሰዱ። እጀ ጠባቡም ከላይ ጀምሮ ወጥ ሆኖ የተሠራ ነበረ እንጂ የተሰፋ አልነበረም።
24 ስለዚህ እርስ በርሳቸው። ለማን እንዲሆን በእርሱ ዕጣ እንጣጣልበት እንጂ አንቅደደው ተባባሉ። ይህም። ልብሴን እርስ በርሳቸው ተከፋፈሉ በእጀ ጠባቤም ዕጣ ተጣጣሉበት የሚለው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ነው።
25 ጭፍሮችም እንዲህ አደረጉ። ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ፥ የእናቱም እኅት፥ የቀለዮጳም ሚስት ማርያም፥ መግደላዊትም ማርያም ቆመው ነበር።
26 ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀ መዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን። አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ አላት።
27 ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን። እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደ ቤቱ ወሰዳት።
28 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ አሁን ሁሉ እንደተፈጸመ አውቆ የመጽሐፉ ቃል ይፈጸም ዘንድ። ተጠማሁ አለ።
29 በዚያም ሆምጣጤ የሞላበት ዕቃ ተቀምጦ ነበር፤ እነርሱም ሆምጣጤውን በሰፍነግ ሞልተው በሁሶፕም አድርገው ወደ አፉ አቀረቡለት።
30 ኢየሱስም ሆምጣጤውን ከተቀበለ በኋላ። ተፈጸመ አለ፥ ራሱንም አዘንብሎ ነፍሱን አሳልፎ ሰጠ።
31 አይሁድም የማዘጋጀት ቀን ስለ ሆነ ያ ሰንበት ትልቅ ነበረና ሥጋቸው በሰንበት በመስቀል ላይ እንዳይኖር፥ ጭናቸውን ሰብረው እንዲያወርዱአቸው ጲላጦስን ለመኑት።
32 ጭፍሮችም መጥተው የፊተኛውን ጭን ከእርሱም ጋር የተሰቀለውን የሌላውን ጭን ሰበሩ፤
33 ወደ ኢየሱስ በመጡ ጊዜ ግን እርሱ ፈጽሞ እንደ ሞተ አይተው ጭኑን አልሰበሩም፤
34 ነገር ግን ከጭፍሮች አንዱ ጎኑን በጦር ወጋው፤ ወዲያውም ደምና ውኃ ወጣ።
35 ያየውም መስክሮአል፤ ምስክሩም እውነት ነው፤ እናንተም ደግሞ ታምኑ ዘንድ እርሱ እውነት እንዲናገር ያውቃል።
36 ይህ የሆነ። ከእርሱ አጥንት አይሰበርም የሚል የመጽሐፉ ቃል እንዲፈጸም ነው።
37 ደግሞም ሌላው መጽሐፍ። የወጉትን ያዩታል ይላል።
38 ከዚህም በኋላ አይሁድን ስለ ፈራ በስውር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የነበረ የአርማትያስ ዮሴፍ የኢየሱስን ሥጋ ሊወስድ ጲላጦስን ለመነ፤ ጲላጦስም ፈቀደለት። ስለዚህም መጥቶ የኢየሱስን ሥጋ ወሰደ።
39 ደግሞም አስቀድሞ በሌሊት ወደ ኢየሱስ መጥቶ የነበረ ኒቆዲሞስ መቶ ንጥር የሚያህል የከርቤና የእሬት ቅልቅል ይዞ መጣ።
40 የኢየሱስንም ሥጋ ወስደው እንደ አይሁድ አገናነዝ ልማድ ከሽቱ ጋር በተልባ እግር ልብስ ከፈኑት።
የዮሐንስ ወንጌል 19 in መጽሐፍ ቅዱስ