13 ብዙ ድውዮችንም ዘይት እየቀቡ ፈወሱአቸው።
14 ስሙም ተገልጦአልና ንጉሡ ሄሮድስ በሰማ ጊዜ። መጥምቁ ዮሐንስ ከሙታን ተነሥቶአል ስለዚህም ኃይል በእርሱ ይደረጋል አለ።
15 ሌሎችም። ኤልያስ ነው አሉ፤ ሌሎችም። ከነቢያት እንደ አንዱ ነቢይ ነው አሉ።
16 ሄሮድስ ግን ሰምቶ። እኔ ራሱን ያስቈረጥሁት ዮሐንስ ይህ ነው እርሱ ከሙታን ተነሥቶአል አለ።
17 ሄሮድስ የወንድሙን የፊልጶስን ሚስት ሄሮድያዳን አግብቶ ነበርና በእርስዋ ምክንያት ራሱ ልኮ ዮሐንስን አስይዞ በወኅኒ አሳስሮት ነበር፤
18 ዮሐንስ ሄሮድስን። የወንድምህ ሚስት ለአንተ ልትሆን አልተፈቀደም ይለው ነበርና።
19 ሄሮድያዳ ግን ተቃውማው ልትገድለው ትፈልግ ነበር አልቻለችም፤
20 ሄሮድስ ዮሐንስ ጻድቅና ቅዱስ ሰው እንደ ሆነ አውቆ ይፈራውና ይጠባበቀው ነበር፤ እርሱንም ሰምቶ በብዙ ነገር ያመነታ ነበር፤
21 በደስታም ይሰማው ነበር። ሄሮድስም በተወለደበት ቀን ለመኳንንቱና ለሻለቆቹ ለገሊላም ሹማምንት ግብር ባደረገ ጊዜ ምቹ ቀን ሆነላትና
22 የሄሮድያዳ ልጅ ገብታ ስትዘፍን ሄሮድስንና ከእርሱ ጋር የተቀመጡትን ደስ አሰኘቻቸው። ንጉሡም ብላቴናይቱን። የምትወጂውን ሁሉ ለምኚኝ እሰጥሽማለሁ አላት፤