13 ሐናንያም መልሶ። ጌታ ሆይ፥ በኢየሩሳሌም በቅዱሳንህ ላይ ስንት ክፉ እንዳደረገ ስለዚህ ሰው ከብዙዎች ሰምቼአለሁ፤
14 በዚህም ስምህን የሚጠሩትን ሁሉ ለማሰር ከካህናት አለቆች ሥልጣን አለው አለ።
15 ጌታም። ይህ በአሕዛብም በነገሥታትም በእስራኤልም ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ፤
16 ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁና አለው።
17 ሐናንያም ሄዶ ወደ ቤቱ ገባ፥ እጁንም ጭኖበት። ወንድሜ ሳውል ሆይ፥ ጌታ፥ እርሱም በመጣህበት መንገድ የታየህ ኢየሱስ ነው፥ ደግሞ ታይ ዘንድና መንፈስ ቅዱስ ይሞላብህ ዘንድ ላከኝ አለ።
18 ወዲያውም እንደ ቅርፊት ያለ ከዓይኑ ወደቀ፥ ያን ጊዜም ደግሞ አየ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፥
19 መብልም በልቶ በረታ። በደማስቆም ካሉት ደቀ መዛሙርት ጋር ጥቂት ቀን ኖረ።
20 ወዲያውም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በምኵራቦቹ ሰበከ።
21 የሰሙትም ሁሉ ተገረሙና። ይህ በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ያጠፋ አይደለምን? ስለዚህስ ታስረው ወደ ካህናት አለቆች ይወስዳቸው ዘንድ ወደዚህ አልመጣምን? አሉ።
22 ሳውል ግን እየበረታ ሄደ፥ በደማስቆም ለተቀመጡት አይሁድ ይህ ክርስቶስ እንደ ሆነ አስረድቶ መልስ ያሳጣቸው ነበር።
23 ብዙ ቀንም ሲሞላ አይሁድ ሊገድሉት ተማከሩ፤
24 ሳውል ግን አሳባቸውን አወቀ። ይገድሉትም ዘንድ በሌሊትና በቀን የከተማይቱን በር ሁሉ ይጠቀብቁ ነበር፤
25 ደቀ መዛሙርት ግን በሌሊት ወስደው በቅጥር ላይ አሳልፈው በቅርጫት አወረዱት።
26 ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርት ጋር ይተባበር ዘንድ ሞከረ፤ ሁሉም ደቀ መዝሙር እንደ ሆነ ስላላመኑ ፈሩት።
27 በርናባስ ግን ወስዶ ወደ ሐዋርያት አገባውና ጌታን በመንገድ እንዴት እንዳየውና እንደ ተናገረው በደማስቆም በኢየሱስ ስም ደፍሮ እንዴት እንደ ነገረ ተረከላቸው።
28 በጌታም በኢየሱስ ስም ደፍሮ እየተናገረ በኢየሩሳሌም ሲወጣና ሲገባ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤
29 ከግሪክ አገርም መጥተው ከነበሩት አይሁድ ጋር ይነጋገርና ይከራከር ነበር፤ እነርሱ ግን ሊገድሉት ፈለጉ።
30 ወንድሞችም ይህን ባወቁ ጊዜ ወደ ቂሣርያ ወሰዱት ወደ ጠርሴስም ሰደዱት።
31 በይሁዳም ሁሉና በገሊላ በሰማርያም የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት በሰላም ኖሩ ታነጹም፤ በእግዚአብሔርም ፍርሃትና በመንፈስ ቅዱስ መጽናናት እየሄዱ ይበዙ ነበር።
32 ጴጥሮስም በየስፍራው ሁሉ ሲዞር በልዳ ወደሚኖሩ ቅዱሳን ደግሞ ወረደ።
33 በዚያም ከስምንት ዓመት ጀምሮ በአልጋ ላይ ተኝቶ የነበረውን ኤንያ የሚሉትን አንድ ሰው አገኘ፤ እርሱም ሽባ ነበረ።
34 ጴጥሮስም። ኤንያ ሆይ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስሃል፤ ተነሣ ለራስህም አንጥፍ አለው።
35 ወዲያውም ተነሣ። በልዳና በሰሮናም የሚኖሩ ሁሉ እርሱን አይተው ወደ ጌታ ዘወር አሉ።
36 በኢዮጴም ጣቢታ የሚሉአት አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፥ ትርጓሜውም ዶርቃ ማለት ነው፤ እርስዋም መልካም ነገር የሞላባት ምጽዋትም የምታደርግ ነበረች።
37 በዚያም ወራት ታመመችና ሞተች፤ አጥበውም በሰገነት አኖሩአት።
38 ልዳም ለኢዮጴ ቅርብ ናትና ደቀ መዛሙርት ጴጥሮስ በዚያ እንዳለ ሰምተው፥ ወደ እነርሱ ከመምጣት እንዳይዘገይ እየለመኑ ሁለት ሰዎች ወደ እርሱ ላኩ።
39 ጴጥሮስም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር መጣ፤ በደረሰም ጊዜ በሰገነት አወጡት መበለቶችም ሁሉ እያለቀሱ ዶርቃ ከእነርሱ ጋር ሳለች ያደረገቻቸውን ቀሚሶችንና ልብሶችን ሁሉ እያሳዩት በፊቱ ቆሙ።
40 ጴጥሮስም ሁሉን ወደ ውጭ አስወጥቶ ተንበርክኮም ጸለየ፥ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ። ጣቢታ ሆይ፥ ተነሺ አላት። እርስዋም ዓይኖችዋን ከፈተች ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ተቀመጠች።