35 ሹምና ፈራጅ እንድትሆን የሾመህ ማን ነው? ብለው የካዱትን፥ ይህን ሙሴን በቍጥቋጦው በታየው በመልአኩ እጅ እግዚአብሔር ሹምና ቤዛ አድርጎ ላከው።
36 ይህ ሰው በግብፅ ምድርና በኤርትራ ባሕር በምድረ በዳም አርባ ዓመት ድንቅና ምልክት እያደረገ አወጣቸው።
37 ይህ ሰው ለእስራኤል ልጆች። እግዚአብሔር ከወንድሞቻችሁ እንደ እኔ ያለ ነቢይ ያስነሣላችኋል፤ እርሱን ስሙት ያላቸው ሙሴ ነው።
38 ይህ ሰው በሲና ተራራ ከተናገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በማኅበሩ ውስጥ የነበረው ነው፤ ይሰጠንም ዘንድ ሕይወት ያላቸውን ቃላት ተቀበለ፤
39 ለእርሱም አባቶቻችን ሊታዘዙት አልወደዱም፤ ነገር ግን ገፉት በልባቸውም ወደ ግብፅ ተመለሱ፤
40 አሮንንም። በፊታችን የሚሄዱ አማልክት ሥራልን፤ ይህ ከግብፅ ምድር ያወጣን ሙሴ ምን እንደ ሆነ አናውቅምና አሉት።
41 በዚያም ወራት ጥጃ አደረጉ ለጣዖቱም መሥዋዕት አቀረቡ፥ በእጃቸውም ሥራ ደስ አላቸው።
42 እግዚአብሔር ግን ዘወር አለ የሰማይንም ጭፍራ ያመልኩ ዘንድ አሳልፎ ሰጣቸው፥ በነቢያትም መጽሐፍ። እናንተ የእስራኤል ቤት፥ አርባ ዓመት በምድረ በዳ የታረደውን ከብትና መሥዋዕትን አቀረባችሁልኝን?