4 ሳትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ከሸጥኸውስ በኋላ በሥልጣንህ አልነበረምን? ይህን ነገር ስለ ምን በልብህ አሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም አለው።
5 ሐናንያም ይህን ቃል ሰምቶ ወደቀ ሞተም፤ በሰሙትም ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ።
6 ጐበዞችም ተነሥተው ከፈኑት አውጥተውም ቀበሩት።
7 ከሦስት ሰዓት ያህል በኋላም ሚስቱ የሆነውን ሳታውቅ ገባች።
8 ጴጥሮስም መልሶ። እስቲ ንገሪኝ፥ መሬታችሁን ይህን ለሚያህል ሸጣችሁትን? አላት። እርስዋም። አዎን፥ ይህን ለሚያህል ነው አለች።
9 ጴጥሮስም። የጌታን መንፈስ ትፈታተኑ ዘንድ ስለ ምን ተስማማችሁ? እነሆ፥ ባልሽን የቀበሩት ሰዎች እግር በደጅ ነው አንቺንም ያወጡሻል አላት።
10 ያን ጊዜም በእግሩ አጠገብ ወደቀች ሞተችም፤ ጐበዞችም ሲገቡ ሞታ አገኙአት አውጥተውም በባልዋ አጠገብ ቀበሩአት።
11 በቤተ ክርስቲያን ሁሉና ይህንም በሰሙ ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሃት ሆነ።
12 በሐዋርያትም እጅ ብዙ ምልክትና ድንቅ በሕዝብ መካከል ይደረግ ነበር፤ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው በሰሎሞን ደጅ መመላለሻ ነበሩ።
13 ከሌሎችም አንድ ስንኳ ሊተባበራቸው የሚደፍር አልነበረም፥
14 ሕዝቡ ግን ያከብሩአቸው ነበር፤ የሚያምኑትም ከፊት ይልቅ ለጌታ ይጨመሩለት ነበር፤ ወንዶችና ሴቶችም ብዙ ነበሩ።
15 ስለዚህም ጴጥሮስ ሲያልፍ ጥላውም ቢሆን ከእነርሱ አንዱን ይጋርድ ዘንድ ድውያንን ወደ አደባባይ አውጥተው በአልጋና በወሰካ ያኖሩአቸው ነበር።