Text copied!
Bibles in Amharic

የሐዋርያት ሥራ 28:13-31 in Amharic

Help us?

የሐዋርያት ሥራ 28:13-31 in መጽሐፍ ቅዱስ

13 ከዚያም እየተዛወርን ወደ ሬጊዩም ደረስን። ከአንድ ቀን በኋላም የደቡብ ነፋስ በነፈሰ ጊዜ በሁለተኛው ቀን ወደ ፑቲዮሉስ መጣን።
14 በዚያም ወንድሞችን አግኝተን በእነርሱ ዘንድ ሰባት ቀን እንድንቀመጥ ለመኑን፤ እንዲሁም ወደ ሮሜ መጣን።
15 ከዚያም ወንድሞች ስለ እኛ ሰምተው እስከ አፍዩስ ፋሩስና ሦስት ማደሪያ እስከሚባለው ሊቀበሉን ወጡ፥ ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገነ ልቡም ተጽናና።
16 ወደ ሮሜም በገባን ጊዜ ጳውሎስ ከሚጠብቀው ወታደር ጋር ለብቻው ይቀመጥ ዘንድ ተፈቀደለት።
17 ከሦስት ቀንም በኋላ ጳውሎስ የአይሁድን ታላላቆች ወደ እርሱ ጠራ፤ በተሰበሰቡም ጊዜ እንዲህ አላቸው። ወንድሞች ሆይ፥ እኔ ሕዝቡን ወይም የአባቶችን ሥርዓት የሚቃወም አንዳች ሳላደርግ፥ ከኢየሩሳሌም እንደ ታሰርሁ በሮማውያን እጅ አሳልፈው ሰጡኝ።
18 እነርሱም መርምረው ለሞት የሚገባ ምክንያት ስላልነበረብኝ ሊፈቱኝ አሰቡ፤
19 አይሁድ ግን በተቃወሙ ጊዜ፥ ወደ ቄሣር ይግባኝ እንድል ግድ ሆነብኝ እንጂ ሕዝቤን የምከስበት ነገር ኖሮኝ አይደለም።
20 ስለዚህም ምክንያት አያችሁና እነግራችሁ ዘንድ ጠራኋችሁ፤ ስለ እስራኤል ተስፋ ይህን ሰንሰለት ለብሻለሁና።
21 እነርሱም። እኛ ከይሁዳ ስለ አንተ ደብዳቤ አልተቀበልንም፥ ከወንድሞችም አንድ ስንኳ መጥቶ ስለ አንተ ክፉ ነገር አላወራልንም ወይም አልተናገረብህም።
22 ነገር ግን ስለዚህ ወገን በየስፍራው ሁሉ እንዲቃወሙ በእኛ ዘንድ ታውቆአልና የምታስበውን ከአንተ እንሰማ ዘንድ እንፈቅዳለን አሉት።
23 ቀንም ቀጥረውለት ብዙ ሆነው ወደ መኖሪያው ወደ እርሱ መጡ፤ ስለ እግዚአብሔር መንግሥትም እየመሰከረ ስለ ኢየሱስም ከሙሴ ሕግና ከነቢያት ጠቅሶ እያስረዳቸው፥ ከጥዋት ጀምሮ እስከ ማታ ድረስ ይገልጥላቸው ነበር።
24 እኵሌቶቹም የተናገረውን አመኑ፥ እኵሌቶቹ ግን አላመኑም፤
25 እርስ በርሳቸውም ባልተስማሙ ጊዜ፥ ጳውሎስ አንዲት ቃል ከተናገረ በኋላ ሄዱ፤ እንዲህም አለ። መንፈስ ቅዱስ በነቢዩ በኢሳይያስ ለአባቶቻችን።
26 ወደዚህ ሕዝብ ሂድና። መስማትን ትሰማላችሁና አታስተውሉም፥ ማየትንም ታያላችሁና አትመለከቱም፤
27 በዓይናቸው እንዳያዩ በጆሮአቸው እንዳይሰሙ በልባቸውም እንዳያስተውሉ ተመልሰውም እንዳልፈውሳቸው፥ የዚህ ሕዝብ ልብ ደንድኖአል ጆሮአቸውም ደንቁሮአል ዓይናቸውንም ጨፍነዋል በላቸው
28 ሲል መልካም ተናገረ። እንግዲህ ይህ የእግዚአብሔር ደኅንነት ለአሕዛብ እንደ ተላከ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፤ እነርሱ ደግሞ ይሰሙታል።
29 ይህንም በተናገረ ጊዜ አይሁድ እርስ በርሳቸው እጅግ እየተከራከሩ ሄዱ።
30 ጳውሎስም በተከራየው ቤት ሁለት ዓመት ሙሉ ተቀመጠ፥ ወደ እርሱም የሚመጡትን ሁሉ ይቀበል ነበር፤
31 ማንም ሳይከለክለው የእግዚአብሔርን መንግሥት እየሰበከ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እጅግ ገልጦ ያስተምር ነበር።
የሐዋርያት ሥራ 28 in መጽሐፍ ቅዱስ