15 ባየኸውና በሰማኸው በሰው ሁሉ ፊት ምስክር ትሆንለታለህና።
16 አሁንስ ለምን ትዘገያለህ? ተነሣና ስሙን እየጠራህ ተጠመቅ ከኃጢአትህም ታጠብ።
17 ወደ ኢየሩሳሌምም ከተመለሱ በኋላ በመቅደስ ስጸልይ ተመስጦ መጣብኝ፥
18 እርሱም። ፍጠን ከኢየሩሳሌምም ቶሎ ውጣ፥ ስለ እኔ የምትመሰክረውን አይቀበሉህምና ሲለኝ አየሁት።
19 እኔም። ጌታ ሆይ፥ በአንተ የሚያምኑትን በምኵራብ ሁሉ እኔ በወኅኒ አገባና እደበድብ እንደ ነበርሁ እነርሱ ያውቃሉ፤
20 የሰማዕትህንም የእስጢፋኖስን ደም ባፈሰሱ ጊዜ፥ ራሴ ደግሞ በአጠገባቸው ስቆም ተስማምቼ የገዳዮችን ልብስ እጠብቅ ነበር አልሁ።
21 እርሱም። ሂድ፥ እኔ ወደ አሕዛብ ከዚህ ወደ ሩቅ እልክሃለሁና አለኝ።
22 እስከዚህም ቃል ድረስ ይሰሙት ነበር፥ ድምፃቸውንም ከፍ አድርገው። እንደዚህ ያለውን ሰው ከምድር አስወግደው፥ በሕይወት ይኖር ዘንድ አይገባውምና አሉ።
23 ሲጮኹና ልብሳቸውን ሲወረውሩ ትቢያንም ወደ ላይ ሲበትኑ፥
24 የሻለቃው ወደ ሰፈሩ እንዲያገቡት አዘዘ፥ እንደዚህም የጮኹበትን ምክንያት ያውቅ ዘንድ። እየገረፋችሁ መርምሩት አላቸው።
25 በጠፍርም በገተሩት ጊዜ ጳውሎስ በአጠገቡ የቆመውን የመቶ አለቃ። የሮሜን ሰው ያለ ፍርድ ትገርፉ ዘንድ ተፈቅዶላችኋልን? አለው።
26 የመቶ አለቃውም በሰማ ጊዜ ወደ ሻለቃው ቀርቦ። ይህ ሰው ሮማዊ ነውና ታደርገው ዘንድ ካለህ ተጠበቅ ብሎ ነገረው።