7 እኛም የባሕሩን መንገድ ጨርሰን ከጢሮስ ወደ አካ ደረስን፥ ለወንድሞችም ሰላምታ ሰጥተን ከእነርሱ ዘንድ አንድ ቀን ተቀመጥን።
8 በነገውም ወጥተን ወደ ቂሣርያ መጣን፥ ከሰባቱም አንድ በሚሆን በወንጌላዊው ፊልጶስ ቤት ገብተን በእርሱ ዘንድ ተቀመጥን።
9 ለእርሱም ትንቢት የሚናገሩ አራት ደናግል ሴቶች ልጆች ነበሩት።
10 አያሌ ቀንም ተቀምጠን ሳለን ነቢይ የነበረ አጋቦስ የሚሉት አንድ ሰው ከይሁዳ ወረደ።
11 ወደ እኛም መጣና የጳውሎስን መታጠቂያ ወስዶ የገዛ እጁንና እግሩን አስሮ። እንዲሁ መንፈስ ቅዱስ። ይህ መታጠቂያ ያለውን ሰው አይሁድ በኢየሩሳሌም እንደዚህ ያስሩታል በአሕዛብም እጅ አሳልፈው ይሰጡታል ይላል አለ።
12 ይህንም በሰማን ጊዜ እኛም በዚያ የሚኖሩትም ወደ ኢየሩሳሌም እንዳይወጣ ለመንነው።
13 ጳውሎስ ግን መልሶ። እያለቀሳችሁ ልቤንም እየሰበራችሁ ምን ማድረጋችሁ ነው? እኔ ስለ ጌታ ስለ ኢየሱስ ስም በኢየሩሳሌም ለመሞት እንኳ ተሰናድቼአለሁ እንጂ ለእስራት ብቻ አይደለም አለ።
14 ምክርንም ሊቀበል እምቢ ባለ ጊዜ። የጌታ ፈቃድ ይሁን ብለን ዝም አልን።
15 ከዚህም ቀን በኋላ ተዘጋጅተን ወደ ኢየሩሳሌም ወጣን።
16 በቂሣርያም ከነበሩ ደቀ መዛሙርት አንዳንዶች ደግሞ ከእኛ ጋር መጡ፥ እነርሱም ወደምናድርበት ወደ ቀደመው ደቀ መዝሙር ወደ ቆጵሮሱ ምናሶን ወደሚሉት ቤት መሩን።
17 ወደ ኢየሩሳሌም በደረስን ጊዜ ወንድሞች በደስታ ተቀበሉን።
18 በነገውም ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ዘንድ ገባ ሽማግሌዎችም ሁሉ መጡ።
19 ሰላምታም ካቀረበላቸው በኋላ በእርሱ ማገልገል እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን በእያንዳንዱ ተረከላቸው።
20 እነርሱም በሰሙ ጊዜ እግዚአብሔርን አመሰገኑ አሉትም። ወንድም ሆይ፥ በአይሁድ መካከል አምነው የነበሩት ስንት አእላፋት እንደ ሆኑ ታያለህ፤ ሁላቸውም ለሕግ የሚቀኑ ናቸው።
21 ልጆቻቸውንም እንዳይገርዙ በሥርዓትም እንዳይሄዱ ብለህ በአሕዛብ መካከል ያሉት አይሁድ ሁሉ ሙሴን ይክዱ ዘንድ እንድታስተምር ስለ አንተ ነግረዋቸዋል።
22 እንግዲህ ምን ይሁን? የአንተን መምጣት ይሰማሉና ብዙዎች የግድ ሳይሰበሰቡ አይቀሩም።