Text copied!
Bibles in Amharic

የሐዋርያት ሥራ 16:3-16 in Amharic

Help us?

የሐዋርያት ሥራ 16:3-16 in መጽሐፍ ቅዱስ

3 ጳውሎስ ይህ ከእርሱ ጋር ይወጣ ዘንድ ወደደ፥ በእነዚያም ስፍራዎች ስለ ነበሩ አይሁድ ይዞ ገረዘው፤ አባቱ የግሪክ ሰው እንደ ሆነ ሁሉ ያውቁ ነበርና።
4 በከተማዎችም ሲዞሩ በኢየሩሳሌም የነበሩት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች የቈረጡትን ሥርዓት ይጠብቁ ዘንድ ሰጡአቸው።
5 አብያተ ክርስቲያናትም በሃያማኖት ይበረቱ ነበር፥ በቍጥርም ዕለት ዕለት ይበዙ ነበር።
6 በእስያም ቃሉን እንዳይናገሩ መንፈስ ቅዱስ ስለ ከለከላቸው በፍርግያና በገላትያ አገር አለፉ፤
7 በሚስያም አንጻር በደረሱ ጊዜ ወደ ቢታንያ ይሄዱ ዘድን ሞከሩ፥ የኢየሱስ መንፈስም አልፈቀደላቸውም፤
8 በሚስያም አጠገብ አልፈው ወደ ጢሮአዳ ወረዱ።
9 ራእይም ለጳውሎስ በሌሊት ታየው፤ አንድ የመቄዶንያ ሰው። ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን እያለ ቆሞ ሲለምነው ነበር።
10 ራእዩንም ካየ በኋላ ወዲያው ወደ መቄዶንያ ልንወጣ ፈለግን፥ ወንጌልን እንሰብክላቸው ዘንድ እግዚአብሔር እንደ ጠራን መስሎናልና።
11 ከጢሮአዳም ተነሥተን በቀጥታ ወደ ሳሞትራቄ በነገውም ወደ ናጱሌ በመርከብ ሄድን፤
12 ከዚያም ወደ ፊልጵስዩስ ደረስን፤ እርስዋም የመቄዶንያ ከተማ ሆና የወረዳ ዋና ከተማና ቅኝ አገር ናት፤ በዚህችም ከተማ አንዳንድ ቀን እንቀመጥ ነበር።
13 በሰንበት ቀንም ከከተማው በር ውጭ የጸሎት ስፍራ በዚያ መሆኑን ስላሰብን ወደ ወንዝ አጠገብ ወጣን፤ ተቀምጠንም ለተሰበሰቡት ሴቶች ተናገርን።
14 ከትያጥሮን ከተማም የመጣች ቀይ ሐር ሻጭ እግዚአብሔርን የምታመልክ ልድያ የሚሉአት አንዲት ሴት ትሰማ ነበረች፤ ጳውሎስም የሚናገረውን ታዳምጥ ዘንድ ጌታ ልብዋን ከፈተላት።
15 እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ። በጌታ የማምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ፥ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ ብላ ለመነችን፤ በግድም አለችን።
16 ወደ ጸሎት ስፍራም ስንሄድ፥ የምዋርተኝነት መንፈስ የነበረባት ለጌቶችዋም እየጠነቈለች ብዙ ትርፍ ታመጣ የነበረች አንዲት ገረድ አገኘችን።
የሐዋርያት ሥራ 16 in መጽሐፍ ቅዱስ