4 ወደ ኢየሩሳሌምም በደረሱ ጊዜ ቤተ ክርስቲያንና ሐዋርያት ሽማግሌዎችም ተቀበሉአቸው፥ እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ያደረገውን ሁሉ አወሩ።
5 ከፈሪሳውያን ወገን ግን ያመኑት አንዳንዶቹ ተነሥተው። ትገርዙአቸው ዘንድና የሙሴን ሕግ እንዲጠብቁ ታዙአቸው ዘንድ ይገባል አሉ።
6 ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ስለዚህ ነገር ለመማከር ተሰበሰቡ።
7 ከብዙ ክርክርም በኋላ ጴጥሮስ ተነሥቶ እንዲህ አላቸው ወንድሞች ሆይ፥ አሕዛብ ከአፌ የወንጌልን ቃል ሰምተው ያምኑ ዘንድ እግዚአብሔር በመጀመሪያው ዘመን ከእናንተ እኔን እንደ መረጠኝ እናንተ ታውቃላችሁ።
8 ልብንም የሚያውቅ አምላክ ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን መንፈስ ቅዱስን በመስጠት መሰከረላቸው፤
9 ልባቸውንም በእምነት ሲያነጻ በእኛና በእነርሱ መካከል አንዳች አልለየም።
10 እንግዲህ አባቶቻችንና እኛ ልንሸከመው ያልቻልነውን ቀንበር በደቀ መዛሙርት ጫንቃ ላይ በመጫን እግዚአብሔርን አሁን ስለ ምን ትፈታተናላችሁ?
11 ነገር ግን በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ እንደ እነርሱ ደግሞ እንድን ዘንድ እናምናለን።
12 ሕዝቡም ሁሉ ዝም አሉ፥ በርናባስና ጳውሎስም እግዚአብሔር በእጃቸው በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ምልክትና ድንቅ ሁሉ ሲተርኩላቸው ይሰሙ ነበር።
13 እነርሱም ዝም ካሉ በኋላ ያዕቆብ እንዲህ ብሎ መለሰ። ወንድሞች ሆይ፥ ስሙኝ።
14 እግዚአብሔር ለስሙ የሚሆንን ወገን ከአሕዛብ ይወስድ ዘንድ አስቀድሞ እንዴት እንደ ጐበኘ ስምዖን ተርኮአል።
15 ከዚህም ጋር የነቢያት ቃል ይሰማማል፥ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ።
16 ከጥንት ጀምሮ ሥራው ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ የታወቀ ነው።