15 ሕግና ነቢያትም ከተነበቡ በኋላ የምኵራቡ አለቆች። ወንድሞች ሆይ፥ ሕዝብን የሚመክር ቃል እንዳላችሁ ተናገሩ ብለው ላኩባቸው።
16 ጳውሎስም ተነሣና በእጁ ጠቅሶ እንዲህ አለ። የእስራኤል ሰዎችና እግዚአብሔርን የምትፈሩት ሆይ፥ ስሙ።
17 የዚህ የእስራኤል ሕዝብ አምላክ አባቶቻችንን መርጦ በግብፅ አገር በእንግድነት ሳሉ ሕዝቡን ከፍ ከፍ አደረጋቸው፥ ከፍ ባለችውም ክንዱ ከዚያ አወጣቸው።
18 በበረሀም አርባ ዓመት ያህል መገባቸው።
19 በከነዓንም አገር ሰባት አሕዛብን አጥፍቶ ምድራቸውን አወረሳቸው።
20 ከዚህም በኋላ እስከ ነቢዩ እስከ ሳሙኤል ድረስ አራት መቶ አምሳ ዓመት ያህል መሳፍንትን ሰጣቸው።