15 በመልካም መሬት ላይም የወደቀ እነርሱ በመልካምና በበጎ ልብ ቃሉን ሰምተው የሚጠብቁት በመጽናትም ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።
16 መብራትንም አብርቶ በዕቃ የሚከድነው ወይም ከአልጋ በታች የሚያኖረው የለም፥ የሚገቡት ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል እንጂ።
17 የማይገለጥ የተሰወረ የለምና፥ የማይታወቅም ወደ ግልጥም የማይመጣ የተሸሸገ የለም።
18 እንግዲህ እንዴት እንድትሰሙ ተጠበቁ፤ ላለው ሁሉ ይሰጠዋልና፥ ከሌለውም ሁሉ፥ ያው ያለው የሚመስለው እንኳ ይወሰድበታል።
19 እናቱና ወንድሞቹም ወደ እርሱ መጡ፥ ከሕዝቡም ብዛት የተነሣ ሊያገኙት አልተቻላቸውም።
20 እናትህና ወንድሞችህ ሊያዩህ ወድደው በውጭ ቆመዋል ብለው ነገሩት።
21 እርሱም መልሶ። እናቴና ወንድሞቼስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚያደርጉት እነዚህ ናቸው አላቸው።
22 ከዕለታቱም በአንዱ እርሱ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ታንኳ ገብቶ። ወደ ባሕር ማዶ እንሻገር አላቸው፤ ተነሡም።
23 ሲሄዱም አንቀላፋ። ዓውሎ ነፋስም በባሕር ላይ ወረደ፥ ውኃውም ታንኳይቱን ይሞላ ነበርና ይጨነቁ ነበር።
24 ቀርበውም። አቤቱ፥ አቤቱ ጠፋን እያሉ አስነሡት። እርሱም ነቅቶ ነፋሱንና የውኃውን ማዕበል ገሠጻቸው፤ ተዉም፥ ጽጥታም ሆነ።
25 እርሱም። እምነታችሁ የት ነው? አላቸው። ፈርተውም ተደነቁ፥ እርስ በርሳቸውም። እንዲህ ነፋሳትንና ውኃን እንኳ የሚያዝ ለእርሱም የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው? አሉ።
26 በገሊላም አንጻር ወዳለችው ወደ ጌርጌሴኖን አገር በታንኳ ደረሱ።
27 ወደ ምድርም በወጣ ጊዜ አጋንንት ያደሩበት አንድ ሰው ከከተማ ወጥቶ ተገናኘው፥ ከብዙ ዘመንም ጀምሮ ልብስ ሳይለብስ በመቃብር እንጂ በቤት አይኖርም ነበር።
28 ኢየሱስንም ባየ ጊዜ ጮኾ በፊቱ ተደፋ በታላቅ ድምፅም። የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳትሣቀየኝ እለምንሃለሁ አለ።
29 ርኵሱን መንፈስ ከሰውዬው እንዲወጣ ያዘው ነበርና። ብዙ ዘመንም ይዞት ነበርና፥ በሰንሰለትና በእግር ብረትም ታስሮ ይጠበቅ ነበር፤ እስራቱንም ሰብሮ በጋኔኑ ወደ ምድረ በዳ ይነዳ ነበር።
30 ኢየሱስም። ስምህ ማን ነው? ብሎ ጠየቀው። እርሱም ብዙዎች አጋንንት ገብተውበት ነበርና። ሌጌዎን አለው።
31 ወደ ጥልቁም ሊሄዱ እንዳያዛቸው ለመኑት።
32 በዚያም በተራራው የብዙ እሪያ መንጋ ይሰማሩ ነበር፤ ወደ እነርሱም ሊገቡ እንዲፈቅድላቸው ለመኑት፤ ፈቀደላቸውም።
33 አጋንንትም ከሰውዬው ወጥተው ወደ እሪያዎች ገቡ፥ መንጋውም ከአፋፉ ወደ ባሕር ተጣደፉና ሰጠሙ።
34 እረኞችም የሆነውን ባዩ ጊዜ ሸሽተው በከተማውና በአገሩ አወሩት።
35 የሆነውን ነገር ሊያዩ ወጥተውም ወደ ኢየሱስ መጡ፥ አጋንንትም የወጡለትን ሰው ለብሶ ልቡም ተመልሶ በኢየሱስ እግር አጠገብ ተቀምጦ አገኙትና ፈሩ።
36 ያዩትም ደግሞ አጋንንት ያደሩበት ሰው እንዴት እንደ ዳነ አወሩላቸው።
37 በዙሪያውም በጌርጌሴኖን አገር ያሉት ሕዝብ ሁሉ ታላቅ ፍርሃት ይዞአቸዋልና ከእነርሱ እንዲሄድ ለመኑት በታንኳም ገብቶ ተመለሰ።
38 አጋንንት የወጡለት ሰውም ከእርሱ ጋር ይኖር ዘንድ ለመነው፤
39 ነገር ግን። ወደ ቤትህ ተመለስ፥ እግዚአብሔር እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረግልህ ንገር ብሎ አሰናበተው። ኢየሱስም እንዴት ያለ ታላቅ ነገር እንዳደረገለት በከተማው ሁሉ እየሰበከ ሄደ።
40 ኢየሱስም በተመለሰ ጊዜ ሁሉ ይጠብቁት ነበርና ሕዝቡ ተቀበሉት።
41 እነሆም፥ ኢያኢሮስ የሚባል ሰው መጣ፥ እርሱም የምኵራብ አለቃ ነበረ በኢየሱስም እግር ላይ ወድቆ ወደ ቤቱ እንዲገባ ለመነው፤
42 አሥራ ሁለት ዓመት የሆናት አንዲት ሴት ልጅ ነበረችውና፤ እርስዋም ለሞት ቀርባ ነበረች። ሲሄድም ሕዝቡ ያጨናንቁት ነበር።
43 ከአሥራ ሁለት ዓመትም ጀምሮ ደም የሚፈሳት ሴት ነበረች፥ ትዳርዋንም ሁሉ ለባለመድኃኒቶች ከስራ ማንም ሊፈውሳት አልተቻለውም።
44 በኋላውም ቀርባ የልብሱን ጫፍ ዳሰሰች፥ የደምዋም ፈሳሽ በዚያን ጊዜ ቆመ።
45 ኢየሱስም። የዳሰሰኝ ማን ነው? አለ። ሁሉም በካዱ ጊዜ፥ ጴጥሮስና ከእርሱ ጋር የነበሩት። አቤቱ፥ ሕዝቡ ያጫንቁሃልና ያጋፉህማል፤ የዳሰሰኝ ማን ነው ትላለህን? አሉ።
46 ኢየሱስ ግን። አንድ ሰው ዳስሶኛል፥ ኃይል ከእኔ እንደ ወጣ እኔ አውቃለሁና አለ።
47 ሴቲቱም እንዳልተሰወረች ባየች ጊዜ እየተንቀጠቀጠች መጥታ በፊቱ ተደፋች፥ በምን ምክንያትም እንደ ዳሰሰችው ፈጥናም እንደ ተፈወሰች በሕዝቡ ሁሉ ፊት አወራች።