23 እርሱም። ያለ ጥርጥር ይህን ምሳሌ። ባለ መድኃኒት ሆይ፥ ራስህን ፈውስ፤ በቅፍርናሆም እንዳደረግኸው የሰማነውን ሁሉ በዚህ በገዛ አገርህ ደግሞ አድርግ ትሉኛላችሁ አላቸው።
24 እንዲህም አለ። እውነት እላችኋለሁ፥ ነቢይ በገዛ አገሩ ከቶ አይወደድም።
25 ነገር ግን እውነት እላችኋለሁ፥ በኤልያስ ዘመን ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሰማይ ተዘግቶ ሳለ በምድር ሁሉ ብርቱ ራብ በነበረ ጊዜ፥ በእስራኤል ብዙ መበለቶች ነበሩ፤
26 ኤልያስም በሲዶና አገር ወዳለች ወደ ሰራፕታ ወደ አንዲት መበለት እንጂ ከእነርሱ ወደ አንዲቱ አልተላከም።
27 በነቢዩ በኤልሳዕ ዘመንም በእስራኤል ብዙ ለምጻሞች ነበሩ፥ ከሶርያዊው ከንዕማን በቀር ከእነርሱ አንድ ስንኳ አልነጻም።
28 በምኵራብም የነበሩ ሁሉ ይህን ሰምተው ቍጣ ሞላባቸው፥ ተነሥተውም ከከተማ ወደ ውጭ አወጡት፥
29 ይጥሉትም ዘንድ ከተማቸው ተሠርታባት ወደ ነበረች ወደ ተራራው አፋፍ ወሰዱት፤
30 እርሱ ግን በመካከላቸው አልፎ ሄደ።