13እነሆም፥ ከእነርሱ ሁለቱ በዚያ ቀን ከኢየሩሳሌም ስድሳ ምዕራፍ ያህል ወደሚርቅ ኤማሁስ ወደሚባል መንደር ይሄዱ ነበር፤
14ስለዚህም ስለ ሆነው ነገር ሁሉ እርስ በርሳቸው ይነጋገሩ ነበር።
15ሲነጋገሩና ሲመራመሩም፥ ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ ከእነርሱ ጋር ይሄድ ነበር፤
16ነገር ግን እንዳያውቁት ዓይናቸው ተይዞ ነበር።
17እርሱም። እየጠወለጋችሁ ስትሄዱ፥ እርስ በርሳችሁ የምትነጋገሩአቸው እነዚህ ነገሮች ምንድር ናቸው? አላቸው።
18ቀለዮጳ የሚባልም አንዱ መልሶ። አንተ በኢየሩሳሌም እንግዳ ሆነህ ለብቻህ ትኖራለህን? በእነዚህ ቀኖች በዚያ የሆነውን ነገር አታውቅምን? አለው።
19እርሱም። ይህ ምንድር ነው? አላቸው። እነርሱም እንዲህ አሉት። በእግዚአብሔርና በሕዝቡ ሁሉ ፊት በሥራና በቃል ብርቱ ነቢይ ስለ ነበረው ስለ ናዝሬቱ ስለ ኢየሱስ፤