Text copied!
Bibles in Amharic

የሉቃስ ወንጌል 22:35-58 in Amharic

Help us?

የሉቃስ ወንጌል 22:35-58 in መጽሐፍ ቅዱስ

35 ደግሞም። ያለ ኮረጆና ያለ ከረጢት ያለ ጫማም በላክኋችሁ ጊዜ፥ አንዳች ጐደለባችሁን? አላቸው። እነርሱም። አንዳች እንኳ አሉ።
36 እርሱም። አሁን ግን ኮረጆ ያለው ከእርሱ ጋር ይውሰድ፥ ከረጢትም ያለው እንዲሁ፤ የሌለውም ልብሱን ሽጦ ሰይፍ ይግዛ።
37 እላችኋለሁና፥ ይህ። ከዓመፀኞች ጋር ተቈጠረ ተብሎ የተጻፈው በእኔ ሊፈጸም ግድ ነው፤ አዎን፥ ስለ እኔ የሚሆነው አሁን ይፈጸማልና አላቸው።
38 እነርሱም። ጌታ ሆይ፥ እነሆ፥ በዚህ ሁለት ሰይፎች አሉ አሉት። እርሱም። ይበቃል አላቸው።
39 ወጥቶም እንደ ልማዱ ወደ ደብረ ዘይት ሄደ፤ ደቀ መዛሙርቱም ደግሞ ተከተሉት።
40 ወደ ስፍራውም ደርሶ። ወደ ፈተና እንዳትገቡ ጸልዩ አላቸው።
41 ከእነርሱም የድንጋይ ውርወራ የሚያህል ራቀ፥ ተንበርክኮም። አባት ሆይ፥
42 ብትፈቅድ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን የእኔ ፈቃድ አይሁን የአንተ እንጂ እያለ ይጸልይ ነበር።
43 ከሰማይም መጥቶ የሚያበረታ መልአክ ታየው።
44 በፍርሃትም ሲጣጣር አጽንቶ ይጸልይ ነበር፤ ወዙም በምድር ላይ እንደሚወርድ እንደ ደም ነጠብጣብ ነበረ።
45 ከጸሎትም ተነሥቶ ወደ ደቀ መዛሙርቱ መጣና ከኀዘን የተነሣ ተኝተው ሲያገኛቸው።
46 ስለ ምን ትተኛላችሁ? ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተነሥታችሁ ጸልዩ አላቸው።
47 ገናም ሲናገር እነሆ፥ ሰዎች መጡ፤ ከአሥራ ሁለቱ አንዱም ይሁዳ የሚባለው ይቀድማቸው ነበር፥ ሊስመውም ወደ ኢየሱስ ቀረበ።
48 ኢየሱስ ግን። ይሁዳ ሆይ፥ በመሳም የሰውን ልጅ አሳልፈህ ትሰጣለህን? አለው።
49 በዙሪያውም የነበሩት የሚሆነውን ባዩ ጊዜ። ጌታ ሆይ፥ በሰይፍ እንምታቸውን? አሉት።
50 ከእነርሱም አንዱ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ቀኝ ጆሮውን ቈረጠው።
51 ኢየሱስ ግን መልሶ። ይህንስ ፍቀዱ አለ፤ ጆሮውንም ዳስሶ ፈወሰው።
52 ኢየሱስም ወደ እርሱ ለመጡበት ለካህናት አለቆችና ለመቅደስ አዛዦች ለሽማግሌዎችም። ወንበዴን እንደምትይዙ ሰይፍና ጐመድ ይዛችሁ ወጣችሁን?
53 በመቅደስ ዕለት ዕለት ከእናንተ ጋር ስሆን እጆቻችሁን አልዘረጋችሁብኝም፤ ይህ ግን ጊዜያችሁና የጨለማው ሥልጣን ነው አላቸው።
54 ይዘውም ወሰዱት ወደ ሊቀ ካህናት ቤትም አገቡት፤ ጴጥሮስም ርቆ ይከተለው ነበር።
55 በግቢ መካከልም እሳት አንድደው በአንድነት ተቀምጠው ሳሉ ጴጥሮስ በመካከላቸው ተቀመጠ።
56 በብርሃኑም በኩል ተቀምጦ ሳለ አንዲት ገረድ አየችውና ትኵር ብላ። ይህ ደግሞ ከእርሱ ጋር ነበረ አለች።
57 እርሱ ግን። አንቺ ሴት፥ አላውቀውም ብሎ ካደ።
58 ከጥቂት ጊዜም በኋላ ሌላው አይቶት። አንተ ደግሞ ከእነርሱ ወገን ነህ አለው። ጴጥሮስ ግን። አንተ ሰው፥ እኔ አይደለሁም አለ።
የሉቃስ ወንጌል 22 in መጽሐፍ ቅዱስ