37 ይህንንም ሲናገር አንድ ፈሪሳዊ ከእርሱ ጋር ምሳ ይበላ ዘንድ ለመነው ገብቶም ተቀመጠ።
38 ከምሳም በፊት አስቀድሞ እንዳልታጠበ ባየው ጊዜ ፈሪሳዊው ተደነቀ።
39 ጌታም እንዲህ አለው። አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጠራላችሁ፥ ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበታል
40 እናንት ደንቆሮዎች፥ የውጭውን የፈጠረ የውስጡን ደግሞ አልፈጠረምን?
41 ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፥ እነሆም፥ ሁሉ ንጹሕ ይሆንላችኋል።
42 ነገር ግን እናንተ ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከጤና አዳም ከአትክልትም ሁሉ አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና እግዚአብሔርን መውደድ ስለምትተላለፉ፥ ወዮላችሁ፤ ነገር ግን ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉት ይገባችሁ ነበር።
43 እናንተ ፈሪሳውያን፥ በምኵራብ የከበሬታ ወንበር በገበያም ሰላምታ ስለምትወዱ፥ ወዮላችሁ።
44 እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ሰዎች ሳያውቁ በላዩ የሚሄዱበት የተሰወረ መቃብር ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ።
45 ከሕግ አዋቂዎችም አንዱ መልሶ። መምህር ሆይ፥ ይህን ማለትህ እኛን ደግሞ መስደብህ ነው አለው።
46 እርሱም እንዲህ አለ። እናንተ ደግሞ ሕግ አዋቂዎች፥ አስቸጋሪ ሸክም ለሰዎች ስለምታሸክሙ፥ ራሳችሁም በአንዲት ጣታችሁ ስንኳ ሸክሙን ስለማትነኩት፥ ወዮላችሁ።
47 አባቶቻችሁ የገደሉአቸውን የነቢያትን መቃብር ስለምትሠሩ፥ ወዮላችሁ።
48 እንግዲህ ለአባቶቻችሁ ሥራ ትመሰክራላችሁ ትስማማላችሁም፤ እነርሱ ገድለዋቸዋልና፥ እናንተም መቃብራቸውን ትሠራላችሁ።
49 ስለዚህ ደግሞ የእግዚአብሔር ጥበብ እንዲህ አለች። ወደ እነርሱ ነቢያትንና ሐዋርያትን እልካለሁ፥ ከእነርሱም ይገድላሉ ያሳድዱማል፥
50 ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የፈሰሰው የነቢያት ሁሉ ደም፥
51 ከአቤል ደም ጀምሮ በመሠዊያውና በቤተ መቅደስ መካከል እስከ ጠፋው እስከ ዘካርያስ ደም ድረስ፥ ከዚህ ትውልድ እንዲፈለግ አዎን እላችኋለሁ፥ ከዚህ ትውልድ ይፈለጋል።
52 እናንተ ሕግ አዋቂዎች፥ የእውቀትን መክፈቻ ስለ ወሰዳችሁ፥ ወዮላችሁ ራሳችሁ አልገባችሁም የሚገቡትንም ከለከላችሁ።