Text copied!
Bibles in Amharic

የሉቃስ ወንጌል 11:24-44 in Amharic

Help us?

የሉቃስ ወንጌል 11:24-44 in መጽሐፍ ቅዱስ

24 ርኵስ መንፈስ ከሰው በወጣ ጊዜ ዕረፍትን እየፈለገ ውኃ በሌለበት ቦታ ያልፋል፤ ባያገኝም። ወደ ወጣሁበት ቤቴ እመለሳለሁ ይላል፤
25 ሲመጣም ተጠርጎ አጊጦም ያገኘዋል።
26 ከዚያ ወዲያ ይሄድና ከእርሱ የከፉትን ሌሎችን ሰባት አጋንንት ከእርሱ ጋር ይይዛል፥ ገብተውም በዚያ ይኖራሉ፤ ለዚያም ሰው ከፊተኛው ይልቅ የኋለኛው ይብስበታል።
27 ይህንም ሲናገር፥ ከሕዝቡ አንዲት ሴት ድምፅዋን ከፍ አድርጋ። የተሸከመችህ ማኅፀንና የጠባሃቸው ጡቶች ብፁዓን ናቸው አለችው።
28 እርሱ ግን። አዎን፥ ብፁዓንስ የእግዚአብሔርን ቃል ሰምተው የሚጠብቁት ናቸው አለ።
29 ብዙ ሕዝብም በተሰበሰቡ ጊዜ እንዲህ ይል ጀመር። ይህ ትውልድ ክፉ ነው፤ ምልክት ይፈልጋል፥ ከነቢዩም ከዮናስ ምልክት በቀር ምልክት አይሰጠውም።
30 ዮናስ ለነነዌ ሰዎች ምልክት እንደ ሆናቸው፥ እንዲሁ ደግሞ የሰው ልጅ ለዚህ ትውልድ ምልክት ይሆናል።
31 ንግሥተ አዜብ በፍርድ ከዚህ ትውልድ ሰዎች ጋር ተነሥታ ትፈርድባቸዋለች፤ የሰሎሞንን ጥበብ ለመስማት ከምድር ዳር መጥታለችና፥ እነሆም፥ ከሰሎሞን የሚበልጥ ከዚህ አለ።
32 የነነዌ ሰዎች በፍርድ ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና፥ እነሆም፥ ከዮናስ የሚበልጥ ከዚህ አለ።
33 መብራትንም አብርቶ በስውር ወይም በእንቅብ በታች የሚያኖረው የለም፥ የሚገቡ ሰዎች ብርሃኑን እንዲያዩ በመቅረዝ ላይ ያኖረዋል እንጂ።
34 የሰውነትህ መብራት ዓይንህ ናት። ዓይንህ ጤናማ በሆነች ጊዜ ሰውነትህ ሁሉ ደግሞ ብሩህ ይሆናል። ዓይንህ ታማሚ በሆነች ጊዜ ግን ሰውነትህ ደግሞ የጨለመ ይሆናል።
35 እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ እንዳይሆን ተመልከት።
36 እንግዲህ ሰውነትህ ሁሉ የጨለማ ቍራጭ የሌለበት ብሩህ ቢሆን፥ መብራት በደመቀ ብርሃን እንደሚያበራልህ በጭራሽ ብሩህ ይሆናል።
37 ይህንንም ሲናገር አንድ ፈሪሳዊ ከእርሱ ጋር ምሳ ይበላ ዘንድ ለመነው ገብቶም ተቀመጠ።
38 ከምሳም በፊት አስቀድሞ እንዳልታጠበ ባየው ጊዜ ፈሪሳዊው ተደነቀ።
39 ጌታም እንዲህ አለው። አሁን እናንተ ፈሪሳውያን የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ ታጠራላችሁ፥ ውስጣችሁ ግን ቅሚያና ክፋት ሞልቶበታል
40 እናንት ደንቆሮዎች፥ የውጭውን የፈጠረ የውስጡን ደግሞ አልፈጠረምን?
41 ነገር ግን በውስጥ ያለውን ምጽዋት አድርጋችሁ ስጡ፥ እነሆም፥ ሁሉ ንጹሕ ይሆንላችኋል።
42 ነገር ግን እናንተ ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከጤና አዳም ከአትክልትም ሁሉ አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና እግዚአብሔርን መውደድ ስለምትተላለፉ፥ ወዮላችሁ፤ ነገር ግን ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉት ይገባችሁ ነበር።
43 እናንተ ፈሪሳውያን፥ በምኵራብ የከበሬታ ወንበር በገበያም ሰላምታ ስለምትወዱ፥ ወዮላችሁ።
44 እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ሰዎች ሳያውቁ በላዩ የሚሄዱበት የተሰወረ መቃብር ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ።
የሉቃስ ወንጌል 11 in መጽሐፍ ቅዱስ