Text copied!
CopyCompare
መጽሐፍ ቅዱስ - የሐዋርያት ሥራ - የሐዋርያት ሥራ 9

የሐዋርያት ሥራ 9:18-41

Help us?
Click on verse(s) to share them!
18ወዲያውም እንደ ቅርፊት ያለ ከዓይኑ ወደቀ፥ ያን ጊዜም ደግሞ አየ፤ ተነሥቶም ተጠመቀ፥
19መብልም በልቶ በረታ። በደማስቆም ካሉት ደቀ መዛሙርት ጋር ጥቂት ቀን ኖረ።
20ወዲያውም ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ በምኵራቦቹ ሰበከ።
21የሰሙትም ሁሉ ተገረሙና። ይህ በኢየሩሳሌም ይህን ስም የሚጠሩትን ያጠፋ አይደለምን? ስለዚህስ ታስረው ወደ ካህናት አለቆች ይወስዳቸው ዘንድ ወደዚህ አልመጣምን? አሉ።
22ሳውል ግን እየበረታ ሄደ፥ በደማስቆም ለተቀመጡት አይሁድ ይህ ክርስቶስ እንደ ሆነ አስረድቶ መልስ ያሳጣቸው ነበር።
23ብዙ ቀንም ሲሞላ አይሁድ ሊገድሉት ተማከሩ፤
24ሳውል ግን አሳባቸውን አወቀ። ይገድሉትም ዘንድ በሌሊትና በቀን የከተማይቱን በር ሁሉ ይጠቀብቁ ነበር፤
25ደቀ መዛሙርት ግን በሌሊት ወስደው በቅጥር ላይ አሳልፈው በቅርጫት አወረዱት።
26ሳውልም ወደ ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ ከደቀ መዛሙርት ጋር ይተባበር ዘንድ ሞከረ፤ ሁሉም ደቀ መዝሙር እንደ ሆነ ስላላመኑ ፈሩት።
27በርናባስ ግን ወስዶ ወደ ሐዋርያት አገባውና ጌታን በመንገድ እንዴት እንዳየውና እንደ ተናገረው በደማስቆም በኢየሱስ ስም ደፍሮ እንዴት እንደ ነገረ ተረከላቸው።
28በጌታም በኢየሱስ ስም ደፍሮ እየተናገረ በኢየሩሳሌም ሲወጣና ሲገባ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤
29ከግሪክ አገርም መጥተው ከነበሩት አይሁድ ጋር ይነጋገርና ይከራከር ነበር፤ እነርሱ ግን ሊገድሉት ፈለጉ።
30ወንድሞችም ይህን ባወቁ ጊዜ ወደ ቂሣርያ ወሰዱት ወደ ጠርሴስም ሰደዱት።
31በይሁዳም ሁሉና በገሊላ በሰማርያም የነበሩት አብያተ ክርስቲያናት በሰላም ኖሩ ታነጹም፤ በእግዚአብሔርም ፍርሃትና በመንፈስ ቅዱስ መጽናናት እየሄዱ ይበዙ ነበር።
32ጴጥሮስም በየስፍራው ሁሉ ሲዞር በልዳ ወደሚኖሩ ቅዱሳን ደግሞ ወረደ።
33በዚያም ከስምንት ዓመት ጀምሮ በአልጋ ላይ ተኝቶ የነበረውን ኤንያ የሚሉትን አንድ ሰው አገኘ፤ እርሱም ሽባ ነበረ።
34ጴጥሮስም። ኤንያ ሆይ፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ይፈውስሃል፤ ተነሣ ለራስህም አንጥፍ አለው።
35ወዲያውም ተነሣ። በልዳና በሰሮናም የሚኖሩ ሁሉ እርሱን አይተው ወደ ጌታ ዘወር አሉ።
36በኢዮጴም ጣቢታ የሚሉአት አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፥ ትርጓሜውም ዶርቃ ማለት ነው፤ እርስዋም መልካም ነገር የሞላባት ምጽዋትም የምታደርግ ነበረች።
37በዚያም ወራት ታመመችና ሞተች፤ አጥበውም በሰገነት አኖሩአት።
38ልዳም ለኢዮጴ ቅርብ ናትና ደቀ መዛሙርት ጴጥሮስ በዚያ እንዳለ ሰምተው፥ ወደ እነርሱ ከመምጣት እንዳይዘገይ እየለመኑ ሁለት ሰዎች ወደ እርሱ ላኩ።
39ጴጥሮስም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር መጣ፤ በደረሰም ጊዜ በሰገነት አወጡት መበለቶችም ሁሉ እያለቀሱ ዶርቃ ከእነርሱ ጋር ሳለች ያደረገቻቸውን ቀሚሶችንና ልብሶችን ሁሉ እያሳዩት በፊቱ ቆሙ።
40ጴጥሮስም ሁሉን ወደ ውጭ አስወጥቶ ተንበርክኮም ጸለየ፥ ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ። ጣቢታ ሆይ፥ ተነሺ አላት። እርስዋም ዓይኖችዋን ከፈተች ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ተቀመጠች።
41እጁንም ለእርስዋ ሰጥቶ አስነሣት፤ ቅዱሳንንና መበለቶችንም ጠራ ሕያውም ሆና በፊታቸው አቆማት።

Read የሐዋርያት ሥራ 9የሐዋርያት ሥራ 9
Compare የሐዋርያት ሥራ 9:18-41የሐዋርያት ሥራ 9:18-41