12ሁሉም ተገረሙና አመንትተው እርስ በርሳቸው። እንጃ ይህ ምን ይሆን? አሉ።
13ሌሎች ግን እያፌዙባቸው። ጉሽ የወይን ጠጅ ጠግበዋል አሉ።
14ነገር ግን ጴጥሮስ ከአሥራ አንዱ ጋር ቆመ፥ ድምፁንም ከፍ አድርጎ እንዲህ ሲል ተናገራቸው። አይሁድ በኢየሩሳሌምም የምትኖሩ ሁላችሁ፥ ይህ በእናንተ ዘንድ የታወቀ ይሁን፥ ቃሎቼንም አድምጡ።
15ለእናንተ እንደ መሰላችሁ እነዚህ የሰከሩ አይደሉም፥ ከቀኑ ሦስተኛ ሰዓት ነውና፤
16ነገር ግን ይህ በነቢዩ በኢዩኤል የተባለው ነው።
17እግዚአብሔር ይላል። በመጨረሻው ቀን እንዲህ ይሆናል፤ ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ፥ ጎበዞቻችሁም ራእይ ያያሉ፥ ሽማግሌዎቻችሁም ሕልም ያልማሉ፤
18ደግሞም በዚያች ወራት በወንዶችና በሴቶች ባሪያዎቼ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ ትንቢትም ይናገራሉ።
19ድንቆችን በላይ በሰማይ፥ ምልክቶችንም በታች በምድር እሰጣለሁ፤ ደምም እሳትም የጢስ ጭጋግም ይሆናል፤
20ታላቅ የሆነ የተሰማም የጌታ ቀን ሳይመጣ ፀሐይ ወደ ጨለማ ጨረቃም ወደ ደም ይለወጣሉ።
21የጌታን ስም የሚጠራም ሁሉ ይድናል።
22የእስራኤል ሰዎች ሆይ፥ ይህን ቃል ስሙ፤ ራሳችሁ እንደምታውቁ፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ እግዚአብሔር በመካከላችሁ በእርሱ በኩል ባደረገው ተአምራትና በድንቆች በምልክቶችም ከእግዚአብሔር ዘንድ ለእናንተ የተገለጠ ሰው ነበረ፤