17እንግዲህ እግዚአብሔር በጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ ላመነው ለእኛ ደግሞ እንደ ሰጠን ያን ስጦታ ለእነርሱ ከሰጠ፥ እግዚአብሔርን ለመከልከል እችል ዘንድ እኔ ማን ነበርሁ?
18ይህን በሰሙ ጊዜም ዝም አሉና። እንኪያስ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐን ሰጣቸው እያሉ እግዚአብሔርን አከበሩ።
19በእስጢፋኖስም ላይ በተደረገው መከራ የተበተኑት እስከ ፊንቄ እስከ ቆጵሮስም እስከ አንጾኪያም ድረስ ዞሩ፥ ቃሉንም ለአይሁድ ብቻ እንጂ ለአንድ ስንኳ አይናገሩም ነበር።
20ከእነርሱ ግን የቆጵሮስና የቀሬና ሰዎች የነበሩት አንዳንዶቹ ወደ አንጾኪያ መጥተው የጌታን የኢየሱስን ወንጌል እየሰበኩ ለግሪክ ሰዎች ተናገሩ።
21የጌታም እጅ ከእነርሱ ጋር ነበረ፤ ቍጥራቸውም እጅግ የሚሆን ሰዎች አምነው ወደ ጌታ ዘወር አሉ።
22ወሬውም በኢየሩሳሌም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ስለ እነርሱ ተሰማ፥ በርናባስንም ወደ አንጾኪያ ላኩት፤
23እርሱም መጥቶ የእግዚአብሔርን ጸጋ ባየ ጊዜ ደስ አለው፥ ሁሉንም በልባቸው ፈቃድ በጌታ ጸንተው ይኖሩ ዘንድ መከራቸው፤
24ደግ ሰውና መንፈስ ቅዱስ እምነትም የሞላበት ነበረና። ብዙ ሕዝብም ወደ ጌታ ተጨመሩ።